ኦሪት ዘዳግም 20
20
ስለ ጦርነት የተሰጠ መመሪያ
1“ጠላቶችህን ለመውጋት ስትዘምት፥ ሠረገሎችንና ፈረሶችን፥ ከአንተ የሚበልጥም ሠራዊት ባየህ ጊዜ ከግብጽ ምድር ያወጣህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ አትፍራቸው፤ 2ጦርነት ከመጀመራችሁ በፊት ካህኑ ወደ ሠራዊቱ ቀርቦ እንዲህ ይበል፦ 3‘የእስራኤል ሰዎች ሆይ! አድምጡ! እነሆ፥ ዛሬ ወደ ጦርነት መሄዳችሁ ነው፤ ከጠላቶቻችሁ የተነሣ አትፍሩ! ወኔአችሁ አይቀዝቅዝ፤ አትሸበሩም! 4እግዚአብሔር አምላካችሁ ከእናንተ ጋር ስለሚሄድ ድልን ያጐናጽፋችኋል።’
5“ከዚህ በኋላ የጦር መሪዎች ለዘማቾች እንዲህ ይበሉ፤ ‘አዲስ ቤት የሠራና አስመርቆ ያልገባበት ሰው በመካከላችሁ ይገኛልን? ይህ ከሆነ እርሱ ወደ ቤቱ ይመለስ፤ እርሱ በጦርነት ላይ ቢሞት ሌላ ሰው ቤቱን አስመርቆ ይገባበታል። 6ወይስ አዲስ የወይን ተክል ተክሎ የመጀመሪያውን ፍሬ ያልሰበሰበ ሰው ይገኛልን? ይህ ከሆነ እርሱ ወደ ቤቱ ይመለስ፤ እርሱ በጦርነት ላይ ቢሞት ወይን ጠጁ ለሌላ ሰው መደሰቻ ይሆናል። 7ሚስት ለማግባትስ ልጃገረድ ያጨ ሰው አለን? ይህ ከሆነ እርሱ ወደ ቤቱ ይመለስ፤ ያለበለዚያ እርሱ በጦርነት ላይ ቢሞት እርሱ ያጫት ልጃገረድ ለሌላ ሰው ሚስት ትሆናለች።’
8“የጦር መሪዎች በሌላም በኩል እንዲህ ብለው ይጠይቁ፥ ‘ወኔ የጐደለው ፈሪ ሰው በመካከላችሁ ይገኛልን? እንዲህ ያለ ሰው ወደ ቤቱ ይመለስ፤ እንዲህ ያለ ሰው የሌሎችን ወኔ ያቀዘቅዛል፤’ 9የጦር መሪዎቹ ለሠራዊቱ ይህን ተናግረው ከጨረሱ በኋላ ለእያንዳንዱ ክፍል አዛዦችን ይምረጡ።
10“በአንዲት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል በምትዘምትበት ጊዜ በመጀመሪያ እንዲገብሩ የሰላም ድርድር ጠይቅ፤ 11የቅጽር በሮቻቸውን ከፍተው እንዲገብሩ የሰላም ድርድርህን ቢቀበሉ በከባድ ሥራ ያገልግሉህ። 12ነገር ግን የዚያች ከተማ ሕዝብ አንገብርም ብለው ከአንተ ጋር መዋጋትን ቢመርጡ፥ ከተማይቱን ክበብ። 13አምላክህ እግዚአብሔር ከተማይቱን ለአንተ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ በውስጥዋ የሚገኙትን ወንዶች ሁሉ ግደል። 14ሆኖም ሴቶችንና ሕፃናት ልጆችን፥ እንስሶችንና በከተማይቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ሁሉ ለራስህ ማርከህ ትወስዳለህ፤ የጠላቶችህ ንብረት የሆነውን ሁሉ ልትጠቀምበት ትችላለህ፤ እግዚአብሔር አምላክህ እርሱን ለአንተ አሳልፎ ሰጥቶሃል። 15እንግዲህ ከምትኖርበት ምድር ርቀው የሚገኙትንና በቅርብ ለሚገኙ ሕዝቦች ንብረት ያልሆኑ ከተሞችን በኀይል በምትይዝበት ጊዜ የምትወስደው እርምጃ ይኸው ነው።
16“እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር የሚገኙትን ከተማዎች በጦርነት በምትይዝበት ጊዜ ግን በውስጣቸው የሚገኘውን ሰው ሁሉ ግደል። 17ስለዚህም በሒታውያን፥ በአሞራውያን፥ በከነዓናውያን፥ በፈሪዛውያን፥ በሒዋውያንና በኢያቡሳውያን ላይ እግዚአብሔር ባዘዛችሁ መሠረት ሕዝቡን በሙሉ ደምስሱ፤ 18ይህንንም የምታደርጉት ለባዕዳን አማልክቶቻቸው ስለ መስገድ አጸያፊ የሆነውን ነገር ሁሉ ለእናንተ በማስተማር እግዚአብሔር የሚጠላውን ኃጢአት እንድትሠሩ እንዳያደርጉአችሁ ነው።
19“አንዲት ከተማ ለመማረክ በምትዘጋጅበት ጊዜ ከበባው ረጅም ጊዜ የወሰደ እንደ ሆነ የዛፎቹ ፍሬ ምግብ ሊሆኑህ ስለሚችሉና ዛፎችም እንደ ሰዎች ከበባ የሚደረግባቸው ስላልሆኑ ዛፎችን አትቊረጥ። የሜዳ ዛፎችን ከበባ የምታደርግባቸው ሰዎች ናቸውን? 20ፍሬ የማያፈሩትን ሌሎች ዛፎች ግን እየቈረጥህ በመከመር ከተማይቱ እስከምትማረክበት ጊዜ ድረስ ለከበባ ተግባር ልትጠቀምባቸው ትችላለህ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 20: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997