ኦሪት ዘዳግም 13
13
1“ ከመካከልህ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ተነሥቶ ‘ተአምር ወይም አስደናቂ ነገር አደርጋለሁ’ ይል ይሆናል። 2አደርጋለሁ ብሎ የተናገረውን ተአምርና ድንቅ ነገር ቢያደርግም እንኳ፥ አንተ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል፤ እናምልካቸውም ቢልህ፥ 3እግዚአብሔር አምላካችሁ በፍጹም ልባችሁ ትወዱት እንደ ሆነ ለማወቅ ፈልጎ ልኮት ይሆናልና ያን ነቢይ ወይም አላሚ አትስሙት። 4አምላካችሁን እግዚአብሔርን ተከተሉት፤ እርሱን ብቻ ፍሩ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቁ፤ ቃሉንም ስሙ፤ እርሱንም አምልኩ፤ ከእርሱም ጋር ያላችሁ አንድነት የጠበቀ ይሁን። 5በባርነት ከኖራችሁባት ከግብጽ ምድር ነጻ በማውጣት በአዳናችሁ በእግዚአብሔር ላይ እንድታምፁ የሚያደርጋችሁን ሕልም አላሚ ወይም ነቢይ ነኝ ባዩን ሁሉ ግደሉ፤ እንደዚህ ያለው ሰው ጸንታችሁ እንድትኖሩበት እግዚአብሔር አምላካችሁ ካዘዛችሁ መንገድ ሊለያችሁ ያቀደ ነው፤ ስለዚህ እናንተ ይህን ክፉ ነገር ከመካከላችሁ አስወግዱ።
6-7“በቅርብም ሆነ በሩቅ ካሉት፥ ከአንዱ የምድር ዳርቻ በአካባቢህ ካሉ ከአሕዛብ አማልክት አንተ ወይም አባቶችህ የማታውቁትን አንዱን እናምልክ በማለት ሌላ እንኳ ቀርቶ የአባትህ፥ ወይም የእናትህ ልጅ ወንድምህ፥ ወንድ ልጅህ፥ ወይም ሴት ልጅህ ወይም የምትወዳት ሚስትህ ወይም የቅርብ ወዳጅህ በምሥጢር ይገፋፋህ ይሆናል። 8ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለውን ሰው ያግባባህ ዘንድ አትፍቀድለት፤ የሚናገረውን እንኳ አታድምጥ፤ ምሕረትም ሆነ ርኅራኄ በማድረግ ሕይወቱን ለማዳን አትሞክር። 9ያለ ማመንታት እንዲሞት አድርግ፤ ይልቁንም በእርሱ ላይ ድንጋይ በመወርወር የመጀመሪያ ሁን፤ ሌላውም ሁሉ ተባብሮ በድንጋይ ወግሮ ይግደለው። 10በባርነት ከኖርክበት ከግብጽ ምድር ነጻ ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ ስለ ሞከረ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው፤ 11ከዚህም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የሆነውን ነገር ሰምተው ይፈራሉ፤ ስለዚህም ያንን ዐይነት ክፉ ነገር እንደገና የሚያደርግ አይኖርም።
12-13“እግዚአብሔር አምላክህ እንድትኖርባቸው ከሰጠህ ከተሞች በአንደኛዋ ውስጥ አንዳንድ ወራዶች ሰዎች ከመካከልህ ተነሥተው ነዋሪዎቹን ወደማታውቃቸው ወደ ሌሎች አማልክት ‘እንሂድና እናምልክ’ ብለው ወደ ጥፋት መንገድ መርተው መውሰዳቸውን ትሰማ ይሆናል፤ 14ይህን በምትሰማበት ጊዜ ስለ ጉዳዩ ጠይቀህ ጠለቅ አድርገህ መርምር፤ ይህ አስከፊ የሆነው ጉዳይ በመካከላችሁ መደረጉ በእውነት ከተረጋገጠ፥ 15በዚያች ከተማ የሚኖሩትን ሰዎች ከከብቶቻቸው ሁሉ ጋር በሙሉ ግደል፤ ያቺንም ከተማ በፍጹም ደምስስ። 16የዚያችን ከተማ ሰዎች ሀብት በሙሉ ሰብስበህ በማምጣት በከተማይቱ አደባባይ እንዲከመር አድርግ፤ ከዚያም በኋላ ከተማይቱንና ሀብቱን ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገህ በእሳት አቃጥለው፤ ዳግመኛም እንዳትሠራ ለዘለዓለም ፍርስራሽ ሆና ትቅር። 17እግዚአብሔር ከአስፈሪ ቊጣው ተመልሶ ምሕረት ያደርግልህ ዘንድ እንዲወድም ከተወሰነው ሀብት አንዳችም ለራስህ አታስቀር፤ ይህን ብታደርግ ለአባቶችህ በመሐላ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ቊጥርህን ያበዛዋል። 18ዛሬ እኔ የሰጠሁህን ትእዛዞች ብትጠብቅና እርሱ ከአንተ የሚፈልገውንም ሁሉ ብታደርግ ይህ ተስፋ በእርግጥ ይፈጸምልሃል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 13: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997