ኦሪት ዘዳግም 14
14
በሐዘን ጊዜ የተከለከለ የለቅሶ ልምድ
1“እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ስለዚህ ለሞተ ሰው በምታዝኑበት ጊዜ ፊታችሁን አትንጩ፤ ጠጒራችሁንም አትላጩ፤ #ዘሌ. 19፥28፤ 21፥5። 2አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተለየህ ሕዝብ ነህ፤ በምድር ላይ ከሚኖሩ ከሌሎች ሕዝቦች መካከል ለእርሱ የተለየህ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ለራሱ መርጦሃል። #ዘፀ. 19፥5-6፤ 4፥20፤ 7፥6፤ 26፥18፤ ቲቶ 2፥14፤ 1ጴጥ. 2፥9።
የሚበሉና የማይበሉ እንስሶች
(ዘሌ. 11፥1-47)
3“ርኩስ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትብሉ፤ 4ስለዚህም ልትበሉአቸው የተፈቀዱላችሁ እንስሶች እነዚህ ናቸው፤ ይኸውም የቀንድ ከብቶችን፥ በጎችንና ፍየሎችን፥ 5አጋዘን ሚዳቋ፥ ቦራይሌ፥ የሜዳ ፍየል፥ ዋላ፥ ድኩላንና ብሖርን ትበላላችሁ። 6በአጠቃላይም ሰኮናቸው የተከፈለና የሚያመሰኩ እንስሶችን ትበላለህ፤ 7ነገር ግን ሰኮናቸው ያልተከፈለውንና የማያመሰኩትን እንስሶች አትብሉ፤ በዚህም ዐይነት ግመል፥ ጥንቸልና ሽኮኮ የመሳሰሉትን አትብሉ፤ እንደነዚህ ያሉት እንስሶች የሚያመሰኩ ቢሆኑም ሰኮናቸው ያልተከፈለ በመሆኑ የረከሱ ሆነው ይቈጠራሉ፤ 8ዐሣማዎችን አትብሉ፤ እነርሱ ሰኮናቸው የተከፈለ ቢሆንም ስለማያመሰኩ የረከሱ ሆነው ይቈጠራሉ፤ እንደነዚህ ያሉትን እንስሶች መብላት ይቅርና በድናቸውን እንኳ አትንኩ።
9“ከዓሣ ዐይነቶችም ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ሁሉ መብላት ትችላላችሁ፤ 10ነገር ግን በውሃ ውስጥ የሚገኘው ክንፍና ቅርፊት የሌለው ፍጥረት ሁሉ አይበላም፤ እንደነዚህ ያሉት እንስሶች በእናንተ ዘንድ የረከሱ ሆነው መቈጠር አለባቸው።
11“ከወፍ ዐይነቶችም ንጹሓን የሆኑትን ትበላላችሁ። 12ሊበሉ የማይገባቸው ግን እነዚህ ናቸው፦ ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ ኣውጭ፥ 13ጭልፊት፥ ጭላት፥ በየወገኑ፥ 14ቊራ በየወገኑ፥ 15ሰጎን፥ ጠላቋ፥ ዝይ፥ በቋል በየወገኑ፥ 16ጒጒት፥ ጋጋኖ፥ የውሃ ዶሮ፥ 17ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ እርኩም 18ሸመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ።
19“ክንፍ ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳት ሁሉ የረከሱ ናቸው፤ እንደነዚህ ያሉት አይበሉም፤ 20ነገር ግን ከእነርሱ መካከል በተለይ ንጹሓን የሆኑትን ትበላላችሁ።
21“ሞቶ የተገኘውን እንስሳ አትብላ፤ በመካከልህ የሚኖሩ የውጪ አገር ሰዎች እንዲመገቡት ፍቀድላቸው፤ ወይም ለውጪ አገር ሰዎች በዋጋ ልትሸጥላቸው ትችላለህ። አንተ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተለየህ ሕዝብ ነህ። #ዘፀ. 23፥19፤ 34፥26።
“የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል።
የዐሥራት አወጣጥ ሕግ
22“በየዓመቱ አርሰህ ከምታገኘው ሰብል ሁሉ ከዐሥር እንዱን እጅ ለይተህ ታስቀምጣለህ፤ 23ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ቦታ የእህልህን፥ የወይን ጠጅህን፥ የዘይትህን ዐሥራት፥ እንዲሁም የከብቶችህንና የበጎችህን በኲራት በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላለህ፤ 24ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ እርሱ ለስሙ መጠሪያ እንዲሆን የመረጠው ቦታ ከአንተ በጣም ሩቅ በመሆኑ ለይተህ ያስቀመጥከውን ዐሥራት ለማጓጓዝ ቢያስቸግርህ፥ 25ዐሥራቱን ሸጠህ ገንዘቡን በመያዝ እግዚአብሔር እንዲመለክበት ወደ መረጠው ቦታ ሂድ። 26እዚያም በገንዘቡ የምተፈልገውን ነገር ከብት፥ ወይም በግ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ጠንካራ መጠጥ፥ ወይም ማንኛውንም የመረጥከውን ነገር ገዝተህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አንተና ቤተሰብህ በመብላት ተደሰቱ።
27“በከተሞችህ የሚኖሩ ሌዋውያን ድርሻ ወይም ርስት ስለሌላቸው እነርሱን ችላ አትበል። 28በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ ከእርሻችሁ ሰብል ሁሉ ከዐሥር አንዱን እያወጣችሁ በከተሞቻችሁ አከማቹ፤ 29በከተሞቻችሁ የሚኖሩ ከእናንተ ጋር የተካፈሉት ርስት የሌላቸው ሌዋውያን፥ የውጪ አገር ስደተኞች፥ እናትና አባት የሌላቸው የሙት ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸው መጥተው ይብሉ፤ ይህን ሁሉ ብታደርጉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምትሠሩት ነገር ሁሉ ይባርካችኋል። #ዘሌ. 27፥30-33፤ ዘኍ. 18፥21።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 14: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997