“እንግዲህ ወደምትወርሱት ምድር ተሻግራችሁ ለመያዝ ኀይል ታገኙ ዘንድ እኔ ዛሬ የማዛችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ። ትእዛዞቹንም ብትጠብቁ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለዘሮቻቸው ሊሰጣቸው ቃል በገባላቸው በማርና በወተት በበለጸገችው፥ በዚያች ለምለም ምድር ለረጅም ዘመን ትኖራላችሁ። ይህች የምትወርሳት ምድር ከዚህ በፊት እንደ ነበርክባት እንደ ግብጽ ምድር አይደለችም። በግብጽ ምድር እህል ከዘራህ በኋላ እንደ ጓሮ አትክልት ማሳውን ውሃ ለማጠጣት ቦዩን በእግርህ አማካይነት ትቈጣጠረው ነበር። ነገር ግን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ የምትወርሱአት ምድር ተራራዎችና ሸለቆዎች ያሉአት ሆና የዝናብ ውሃ የምትጠጣ ናት። ይህችን ምድር የሚንከባከባትና ዓመቱን ሙሉ የሚጠብቃት እግዚአብሔር አምላክህ ነው። “ስለዚህም ዛሬ እኔ የማዛችሁን ሕግ ሁሉ ጠብቁ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁንም ውደዱ፤ በፍጹም ልባችሁም አገልግሉት። ይህን ብታደርጉ እግዚአብሔር የክረምቱንና የበልጉን ዝናብ በወቅቱ ለምድራችሁ ይልካል፤ በዚህም ዐይነት ለእናንተ ሲሳይ የሚሆነው እህል፥ ወይን ጠጅና የወይራ ዘይት፥ እንስሶችህ የሚመገቡት ሣር ይበዛላችኋል፤ የሚያስፈልግህን ምግብ ሁሉ ታገኛለህ። ከእግዚአብሔር ርቃችሁ ባዕዳን አማልክትን ለመከተልና ለማምለክ ዘወር እንዳትሉ ተጠንቀቁ። ይህን ብታደርጉ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይቈጣል፤ ሰማያትን ዘግቶ ምድሪቱን ዝናብ እንዳይዘንብባትና ፍሬ እንዳትሰጥ ያደርጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር ከሚሰጣችሁ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ። “እነዚህን ትእዛዞች ዘወትር በልቡናችሁና በአእምሮአችሁ ቅረጹአቸው፤ መታሰቢያም ይሆኑላችሁ ዘንድ እነርሱን በክንዳችሁ ላይ እሰሩ፤ በግንባራችሁም ላይ እንደማስታወሻ አኑሩአቸው፤ ለልጆቻችሁም አስተምሩአቸው፤ በቤት በምትቀመጡበት ጊዜ፥ ወይም ስትሄዱ፥ ዕረፍት በምታደርጉበትም ሆነ በምትሠሩበት ጊዜ ሁሉ ስለ እነርሱ ተነጋገሩ፤ በቤትህ የበር መቃኖችና በቅጽር በሮችህም ሳንቃ ላይ ጻፋቸው። ይህን ብታደርግ እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ ሊሰጣቸው በመሐላ ቃል በገባላቸው ምድር የአንተና የልጆችህ ዘመን ከምድር በላይ እንዳለው ሰማይ ይረዝማል። “ስለዚህም እኔ የሰጠኋችሁን ትእዛዞች በጥንቃቄ ፈጽሙ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁን ውደዱ፤ በእርሱ መንገድም በመጓዝ ለእርሱ ታማኞች ሁኑ። ይህን ብታደርጉ እግዚአብሔር እነዚህን በፊታችሁ ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ያስወጣል፤ እናንተም በብዛትና በኀይል ከእናንተ እጅግ ብርቱዎች የሆኑትን ሕዝቦች ምድር ትወርሳላችሁ። ስታልፉ በእግራችሁ የምትረግጡት መሬት ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም በደቡብ በኩል ካለው በረሓ ተነሥቶ በሰሜን በኩል እስካሉት እስከ ሊባኖስ ተራራዎች፥ እንዲሁም በምሥራቅ በኩል ከሚገኘው ከኤፍራጥስ ወንዝ ተነሥቶ በምዕራብ በኩል እስከሚገኘው እስከ ታላቁ ሜዲቴራኒያን ባሕር ድረስ ይሰፋል። በዚያች ምድር በምትሄዱበት ስፍራ ሁሉ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ሕዝቦች ሁሉ እንዲፈሩአችሁ ያደርጋል፤ ሊቋቋማችሁ የሚችልም ከቶ አይገኝም። “እነሆ! እኔ ዛሬ ከበረከትና ከመርገም አንዱን እንድትመርጡ ዕድል እሰጣችኋለሁ። ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን የእግዚአብሔር አምላካችሁን ትእዛዞች ሁሉ ብትፈጽሙ በረከት ታገኛላችሁ፤ ከዚህ በፊት ያላወቃችኋቸውን ባዕዳን አማልክት ወደ መከተል አዘንብላችሁ እነዚህን ትእዛዞች ባትፈጽሙ ግን ርግማን ይመጣባችኋል። እግዚአብሔር ወደምትወርሳት ምድር በሚያስገባህ ጊዜ በረከቱን በገሪዛን ተራራ፥ መርገሙንም በዔባል ተራራ ታውጃለህ። እነዚህም ተራራዎች ከዮርዳኖስ ማዶ በስተምዕራብ በኩል፥ በአራባ በሚኖሩት በከነዓናውያንም ምድር በጌልገላ ፊት ለፊት ከሞሬ ዛፍ አጠገብ የሚገኙ ናቸው። አምላካችሁ እግዚአብሔር እንድትኖሩባት የሰጣችሁን ምድር ለመውረስ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁና ወርሳችሁም በምትኖሩባት ጊዜ፥ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ሕግና ሥርዓት ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቁ።
ኦሪት ዘዳግም 11 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘዳግም 11:8-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች