የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 11

11
መታዘዝ የሚያስገኘው ጥቅም
1“እንግዲህ እግዚአብሔር አምላክህን ውደድ፤ እርሱ ከአንተ የሚፈልገውን ሥርዓቱን፥ ደንቡንና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ፈጽም። 2ልጆቻችሁ ያላዩትና የማያውቁት ቢሆኑም እንኳ፥ እናንተ ዛሬ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ፥ ታላቅነቱን፥ ኀይሉንና ሥልጣኑን ያያችሁ መሆኑን አስታውሱ። 3ተአምራቱንና እርሱ በግብጽ ንጉሥና በመላው አገሩ ላይ ያደረገውን ድንቅ ሥራ ሁሉ አይታችኋል። #ዘፀ. 7፥8—12፥13። 4እናንተን ባሳደዱአችሁ ጊዜ የግብጽን ሠራዊት ከነፈረሶቻቸውና ከነሠረገሎቻቸው በቀይ ባሕር በማስጠም እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ለዘለቄታው እንደ ደመሰሳቸው አይታችኋል። #ዘፀ. 14፥28። 5እዚህ ከመድረሳችሁም በፊት እግዚአብሔር በዚያ በረሓ ምን እንዳደረገ ታውቃላችሁ። 6ከሮቤል ነገድ ወገን የኤልያብ ልጆች በሆኑት በዳታንና በአቤሮን ላይ ያደረገውን አስታውሱ፤ እስራኤላውያን ሁሉ በዐይናቸው እያዩ መሬት ተከፍታ እነርሱንና ቤተሰቦቻቸውን፥ ድንኳኖቻቸውንና ሕይወት ያለውና የእነርሱ የነበረውን ሁሉ ዋጠቻቸው። #ዘኍ. 16፥31-32። 7እግዚአብሔር ያደረጋቸውን እነዚህን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ በዐይናችሁ ያያችሁ እናንተ ራሳችሁ ናችሁ።
የተስፋይቱ ምድር በረከት
8“እንግዲህ ወደምትወርሱት ምድር ተሻግራችሁ ለመያዝ ኀይል ታገኙ ዘንድ እኔ ዛሬ የማዛችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ። 9ትእዛዞቹንም ብትጠብቁ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለዘሮቻቸው ሊሰጣቸው ቃል በገባላቸው በማርና በወተት በበለጸገችው፥ በዚያች ለምለም ምድር ለረጅም ዘመን ትኖራላችሁ። 10ይህች የምትወርሳት ምድር ከዚህ በፊት እንደ ነበርክባት እንደ ግብጽ ምድር አይደለችም። በግብጽ ምድር እህል ከዘራህ በኋላ እንደ ጓሮ አትክልት ማሳውን ውሃ ለማጠጣት ቦዩን በእግርህ አማካይነት ትቈጣጠረው ነበር። 11ነገር ግን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ የምትወርሱአት ምድር ተራራዎችና ሸለቆዎች ያሉአት ሆና የዝናብ ውሃ የምትጠጣ ናት። 12ይህችን ምድር የሚንከባከባትና ዓመቱን ሙሉ የሚጠብቃት እግዚአብሔር አምላክህ ነው።
13“ስለዚህም ዛሬ እኔ የማዛችሁን ሕግ ሁሉ ጠብቁ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁንም ውደዱ፤ በፍጹም ልባችሁም አገልግሉት። 14ይህን ብታደርጉ እግዚአብሔር የክረምቱንና የበልጉን ዝናብ በወቅቱ ለምድራችሁ ይልካል፤ በዚህም ዐይነት ለእናንተ ሲሳይ የሚሆነው እህል፥ ወይን ጠጅና የወይራ ዘይት፥ 15እንስሶችህ የሚመገቡት ሣር ይበዛላችኋል፤ የሚያስፈልግህን ምግብ ሁሉ ታገኛለህ። 16ከእግዚአብሔር ርቃችሁ ባዕዳን አማልክትን ለመከተልና ለማምለክ ዘወር እንዳትሉ ተጠንቀቁ። 17ይህን ብታደርጉ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይቈጣል፤ ሰማያትን ዘግቶ ምድሪቱን ዝናብ እንዳይዘንብባትና ፍሬ እንዳትሰጥ ያደርጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር ከሚሰጣችሁ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ። #ዘሌ. 26፥3-5፤ ዘዳ. 7፥12-16፤ 28፥1-14።
18“እነዚህን ትእዛዞች ዘወትር በልቡናችሁና በአእምሮአችሁ ቅረጹአቸው፤ መታሰቢያም ይሆኑላችሁ ዘንድ እነርሱን በክንዳችሁ ላይ እሰሩ፤ በግንባራችሁም ላይ እንደማስታወሻ አኑሩአቸው፤ 19ለልጆቻችሁም አስተምሩአቸው፤ በቤት በምትቀመጡበት ጊዜ፥ ወይም ስትሄዱ፥ ዕረፍት በምታደርጉበትም ሆነ በምትሠሩበት ጊዜ ሁሉ ስለ እነርሱ ተነጋገሩ፤ 20በቤትህ የበር መቃኖችና በቅጽር በሮችህም ሳንቃ ላይ ጻፋቸው። #ዘዳ. 6፥6-9። 21ይህን ብታደርግ እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ ሊሰጣቸው በመሐላ ቃል በገባላቸው ምድር የአንተና የልጆችህ ዘመን ከምድር በላይ እንዳለው ሰማይ ይረዝማል።
22“ስለዚህም እኔ የሰጠኋችሁን ትእዛዞች በጥንቃቄ ፈጽሙ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁን ውደዱ፤ በእርሱ መንገድም በመጓዝ ለእርሱ ታማኞች ሁኑ። 23ይህን ብታደርጉ እግዚአብሔር እነዚህን በፊታችሁ ያሉትን ሕዝቦች ሁሉ ያስወጣል፤ እናንተም በብዛትና በኀይል ከእናንተ እጅግ ብርቱዎች የሆኑትን ሕዝቦች ምድር ትወርሳላችሁ። 24ስታልፉ በእግራችሁ የምትረግጡት መሬት ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም በደቡብ በኩል ካለው በረሓ ተነሥቶ በሰሜን በኩል እስካሉት እስከ ሊባኖስ ተራራዎች፥ እንዲሁም በምሥራቅ በኩል ከሚገኘው ከኤፍራጥስ ወንዝ ተነሥቶ በምዕራብ በኩል እስከሚገኘው እስከ ታላቁ ሜዲቴራኒያን ባሕር ድረስ ይሰፋል። 25በዚያች ምድር በምትሄዱበት ስፍራ ሁሉ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ሕዝቦች ሁሉ እንዲፈሩአችሁ ያደርጋል፤ ሊቋቋማችሁ የሚችልም ከቶ አይገኝም። #ኢያሱ 1፥3-5።
26“እነሆ! እኔ ዛሬ ከበረከትና ከመርገም አንዱን እንድትመርጡ ዕድል እሰጣችኋለሁ። 27ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን የእግዚአብሔር አምላካችሁን ትእዛዞች ሁሉ ብትፈጽሙ በረከት ታገኛላችሁ፤ 28ከዚህ በፊት ያላወቃችኋቸውን ባዕዳን አማልክት ወደ መከተል አዘንብላችሁ እነዚህን ትእዛዞች ባትፈጽሙ ግን ርግማን ይመጣባችኋል። 29እግዚአብሔር ወደምትወርሳት ምድር በሚያስገባህ ጊዜ በረከቱን በገሪዛን ተራራ፥ መርገሙንም በዔባል ተራራ ታውጃለህ። #ዘዳ. 27፥11-14፤ ኢያሱ 8፥33-35። 30እነዚህም ተራራዎች ከዮርዳኖስ ማዶ በስተምዕራብ በኩል፥ በአራባ በሚኖሩት በከነዓናውያንም ምድር በጌልገላ ፊት ለፊት ከሞሬ ዛፍ አጠገብ የሚገኙ ናቸው። 31አምላካችሁ እግዚአብሔር እንድትኖሩባት የሰጣችሁን ምድር ለመውረስ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁና ወርሳችሁም በምትኖሩባት ጊዜ፥ 32ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ሕግና ሥርዓት ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ