ኦሪት ዘዳግም 10
10
ሙሴ ዐሥሩን ትእዛዞች እንደገና መቀበሉ
(ዘፀ. 34፥1-10)
1ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ቀድሞ የተሰበሩትን የድንጋይ ጽላቶች አስመስለህ በምትካቸው ሁለት ጽላቶች ቅረጽ፤ ለእነርሱ ማኖሪያ የሚሆን ታቦትም ከእንጨት ሥራ፤ እኔም ወዳለሁበት ተራራ ውጣ፤ 2ቀድሞ በሰበርካቸው ጽላቶች ላይ የነበሩትን ትእዛዞች እንደገና እጽፍባቸዋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታኖራቸዋለህ።”
3“ስለዚህም እኔ ከግራር እንጨት ታቦትን ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ያሉትንም የድንጋይ ጽላቶች በመቅረጽ አዘጋጀሁ፤ እነርሱንም በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ፤ 4እግዚአብሔርም በተራራው ግርጌ ተሰብስባችሁ በነበረበት ቀን በእሳት ውስጥ ሆኖ የገለጠላችሁን ዐሥሩን ትእዛዞች እንደ ቀድሞው ጽሑፍ አድርጎ በአሁኖቹ ጽላቶች ላይ ጻፈ፤ ጽላቶቹንም ለእኔ ሰጠኝ፤ 5እኔም ከተራራው ተመልሼ በመውረድ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት ጽላቶቹን በሠራሁት ታቦት ውስጥ አኖርኳቸው፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እነሆ፥ በዚያው ውስጥ ይገኛሉ።”
6(እስራኤላውያንም ከቤን ያዕቃን የውሃ ጒድጓዶች ተነሥተው ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም በዚያው ሞቶ ተቀበረ፤ በእርሱም ምትክ ልጁ አልዓዛር ካህን ሆነ። #ዘኍ. 20፥28፤ 33፥38። 7ከዚያም ተነሥተው ጉድጎዳ ተብሎ ወደሚጠራ ስፍራ ተጓዙ፤ ከዚያም የውሃ ፈሳሾች ወደሚገኙበት ወደ ዮጥባታ አመሩ፤ 8በዚያን ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት እንዲሸከሙ፥ በፊቱም በመቆም እንዲያገለግሉትና ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም እንዲባርኩ የሌዊን ነገድ በመለየት ሾመ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የሌዊ ነገድ ትውልድ አገልግሎት ይኸው ነው። #ዘኍ. 3፥5-8። 9የሌዊ ነገድ ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር ርስት እንዲኖረው ያልተደረገበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ አስቀድሞ እንደ ተናገረ ካህናት ሆነው የማገልገልን መብት በማግኘታቸው ራሱ እግዚአብሔር ለሌዋውያን ርስታቸው ነው።)
10“እኔም ከዚህ በፊት ባደረግሁት ዐይነት እንደገና በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመጸለይ ቈየሁ፤ እግዚአብሔርም እንደገና ልመናዬን ሰምቶ አንተን ላለማጥፋት ፈቀደ። #ዘፀ. 34፥28። 11ከዚህም በኋላ ‘እንግዲህ ሂድ፤ ለቀድሞ አባቶቻቸው በሰጠሁት የተስፋ ቃል መሠረት ምድሪቱን እንዲወርሱ ሕዝቡን ምራ’ አለኝ።
ከእናንተ የሚፈለገው እግዚአብሔርን መፍራት ነው
12-13“እንግዲህ እስራኤል ሆይ! እግዚአብሔር አምላክህን እንድትፈራው፥ በመንገዱ ሁሉ እንድትሄድ፥ እንድትወደው በሙሉ ልብህና በሙሉ ሐሳብህ እንድታመልከው፥ ለደኅንነትህ ሲባል እኔ ዛሬ የማዝህን የእግዚአብሔር አምላክህን ትእዛዝና ድንጋጌ እንድትጠብቅ ነው እንጂ እርሱ ሌላ ከአንተ ምን ይፈልጋል? 14ሰማይና ከሰማይ በላይ ያሉ ሰማያት፥ ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ማናቸውም ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው። 15እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶችህ የነበረው ፍቅር እጅግ ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ፥ ዛሬም አንተን ከብዙ አሕዛብ መካከል መርጦአል፤ አንተም እስከ አሁን የእርሱ ምርጥ ሕዝብ ነህ። 16ስለዚህም ከአሁን በኋላ ልበ ደንዳናነትንና እልኸኛነትን አስወግዳችሁ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ 17እግዚአብሔር አምላካችሁ ከባዕዳን አማልክት ሁሉና ከኀይላትም ሁሉ በላይ ታላቅና ብርቱ ስለ ሆነ በፍርሃት መከበር ይገባዋል። እርሱ በፍርድ አያዳላም፤ ጉቦም አይቀበልም። #1ጢሞ. 6፥15፤ ራዕ. 17፥14፤ 19፥16፤ ሐ.ሥ. 10፥34፤ ሮም 2፥11፤ ገላ. 2፥6፤ ኤፌ. 6፥9። 18እርሱ እናትና አባት ለሌላቸው ድኻ አደጎችና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች በትክክል ይፈርዳል፤ እርሱ በእኛ ሕዝብ መካከል የሚኖሩትንም መጻተኞች ሁሉ ስለሚወድ ምግብና ልብስ ይሰጣቸዋል። 19ስለዚህም እናንተም ለእነዚህ ስደተኞች ፍቅራችሁን ልታሳዩአቸው ይገባል፤ እናንተም ራሳችሁ በግብጽ ምድር መጻተኞች የሆናችሁበት ጊዜ ነበር። 20አምላክህን እግዚአብሔርን በመፍራት ለእርሱ ታዘዝ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤ ለእርሱ ታማኝ ሆነህ በእርሱ ስም ብቻ ማል። 21እርሱ አምላክህ ነው፤ እርሱ ለአንተ ያደረገልህን ታላላቅና አስደናቂ ነገሮችን ሁሉ በገዛ ዐይኖችህ ስላየህ ዘወትር አመስግነው። 22የቀድሞ አባቶችህ ወደ ግብጽ በወረዱ ጊዜ ብዛታቸው ሰባ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር አምላክህ የአንተን ቊጥር ብዛት እንደ ሰማይ ከዋክብት አድርጎታል። #ዘፍ. 15፥5፤ 22፥17፤ 46፥27።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997