ትንቢተ ዳንኤል 7:15-27

ትንቢተ ዳንኤል 7:15-27 አማ05

“እኔ ዳንኤል ባየሁት ራእይ ተጨንቄ መንፈሴ ታወከ። እዚያም ቆመው ከነበሩት ወደ አንዱ ቀረብ ብዬ የዚህን ሁሉ እውነት ትርጒም ጠየቅሁት፤ እርሱም የዚህን ሁሉ ትርጒም ነገረኝ። እንዲህም አለኝ፦ ‘እነዚህ አራት ታላላቅ አውሬዎች በምድር ላይ የሚነሡ አራት መንግሥታት ናቸው። ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን መንግሥቱን ወርሰው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የራሳቸው እንዲሆን ያደርጉታል።’ “ከዚህ በኋላ ከሌሎቹ አውሬዎች ሁሉ ልዩ ስለ ነበረው ስለ አራተኛው አውሬ በይበልጥ ለማወቅ ፈለግኹ፤ ይህ አውሬ እጅግ አስፈሪ የሆነ፥ ዐድኖ ያገኘውን ሁሉ በብረት ጥርሶቹና በነሐስ ጥፍሮቹ ሰባብሮና ቦጫጭቆ የሚበላ፥ የተረፈውንም በእግሩ የሚረጋግጥ ነበር። ደግሞም በዚህ አውሬ ራስ ላይ ስለ ነበሩት ዐሥር ቀንዶችና በኋላ ስለ በቀለው ትንሽ ቀንድ፥ እንዲሁም ለትንሹ ቀንድ ቦታ ለመተው ተነቃቅለው ስለ ወደቁት ሦስት ቀንዶች ለማወቅ ፈለግኹ። ይህ ትንሽ ቀንድ ዐይኖችና አፍ ነበረው፤ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ አስፈሪ ሆኖ በትዕቢት ይናገር ነበር። “እኔም በመመልከት ላይ ሳለሁ ያ ትንሽ ቀንድ በእግዚአብሔር ቅዱሳን ላይ ጦርነት አስነሥቶ ድል አደረጋቸው። ይህም የሆነው ዘለዓለማዊው መጥቶ ለልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን ፍትሕ እስከ ሰጠበት ጊዜ ድረስ ነው፤ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወርሱበት ጊዜ ደረሰ። “እርሱም ትርጒሙን እንዲህ ሲል አስረዳኝ፤ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛ መንግሥት ነው፤ ይህ መንግሥት ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ በመሆኑ ምድርን ሁሉ በመውረር ረግጦና ቀጥቅጦ ይገዛል። ዐሥሩ ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡት ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያን በኋላ ከበፊተኞቹ ነገሥታት የተለየ ሌላ ንጉሥ ተነሥቶ ከዐሥሩ መንግሥታት ሦስቱን ይገለብጣል፤ በልዑል እግዚአብሔር ላይ በመታበይ ይናገራል፤ የልዑል እግዚአብሔርንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ የተቀደሱ በዓላትንና ሕጉን ለመለወጥ ያቅዳል፤ ቅዱሳኑም ለሦስት ዓመት ተኩል በእርሱ ሥልጣን ሥር ይሆናሉ። ከዚያን በኋላ የፍርድ ዙፋን ይዘረጋል፤ እርሱም መንግሥታዊ ሥልጣኑን ተገፎ ለዘለዓለም ይደመሰሳል፤ ከሰማይ ሁሉ በታች በምድር ላይ ያለ የመንግሥት ሥልጣን፥ ኀይልና ገናናነት ሁሉ ለልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን ይሰጣል፤ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የዓለም ግዛቶች ሁሉም ለእነርሱ በመታዘዝ ያገለግሉአቸዋል።’ ”