“እኔ ዳንኤል በመንፈሴ ታወክሁ፤ ያየሁትም ራእይ እጅግ አስጨነቀኝ። በዚያ ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ፣ የዚህ ሁሉ እውነተኛ ትርጕም ምን እንደ ሆነ ጠየቅሁት። “እርሱም መለሰልኝ፤ የእነዚህንም ነገሮች ትርጕም እንዲህ ሲል ነገረኝ፤ ‘አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ መንግሥታት ናቸው፤ ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ ለዘላለምም ይይዙታል፤ አዎን፤ ለዘላለም ይይዙታል።’ “ከዚያም የሚያደቅቀውንና የሚበላውን፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ የሚረጋግጠውን፣ የብረት ጥርሶችና የናስ ጥፍሮች የነበሩትን፣ ከሌሎቹ አራዊት የተለየና እጅግ አስፈሪ የሆነውን የአራተኛውን አውሬ እውነተኛ ትርጕም ማወቅ ፈለግሁ። ደግሞም በራሱ ላይ ስላሉት ዐሥር ቀንዶች፣ ከመካከላቸው ብቅ ስላለው ቀንድና ከዚሁ ቀንድ ፊት ስለ ተነቃቀሉት ሦስት ቀንዶች፣ እንደዚሁም ከሌሎች ስለ በለጠው የሰው ዐይኖች የሚመስሉ ዐይኖች፣ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ስለ ነበሩት ስለዚሁ ቀንድ ማወቅ ፈለግሁ። እነሆም፤ ይህ ቀንድ በቅዱሳን ላይ ጦርነት ዐውጆ አሸነፋቸው፤ ይህም የሆነው ጥንታዌ ጥንቱ እስኪመጣና ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪፈርድላቸው ድረስ ነበር፤ ከዚያም የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን የሚወርሱበት ዘመን መጣ። “እርሱም እንዲህ አለኝ፣ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛው መንግሥት ነው። ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፤ መላውንም ምድር እየረገጠና እያደቀቀ ይበላል። ዐሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚወጡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከዚያም በኋላ ከእነርሱ የተለየ ሌላ ንጉሥ ይነሣል፤ ሦስቱንም ነገሥታት ያንበረክካል። በልዑል ላይ የዐመፅ ቃል ይናገራል፤ የልዑልንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ ለበዓላት የተመደበውን ጊዜና ሕግን ለመለወጥ ይሞክራል፤ ቅዱሳንም ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታም ለርሱ ዐልፈው ይሰጣሉ። “ ‘ነገር ግን የፍርድ ዙፋን ይዘረጋል፤ ሥልጣኑም ይወሰድበታል፤ ፈጽሞ ለዘላለም ይደመሰሳል። ከዚያም ከሰማይ በታች ያሉ መንግሥታት ልዕልና፣ ሥልጣንና ታላቅነት ለልዑሉ ሕዝብ፣ ለቅዱሳን ይሰጣል። መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ይሆናል፤ ገዦች ሁሉ ያመልኩታል፤ ይታዘዙታልም።’
ዳንኤል 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ዳንኤል 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዳንኤል 7:15-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች