ትንቢተ ዳንኤል 6:1-13

ትንቢተ ዳንኤል 6:1-13 አማ05

ዳርዮስ በመንግሥቱ ግዛት ሁሉ ላይ እንዲያስተዳድሩ መቶ ኻያ አገረ ገዢዎች ለመሾም ፈለገ። በተጨማሪም የንጉሡ ቅርብ ረዳቶች ሆነው ንጉሡ ምንም ነገር እንዳይጐድልበት አገረ ገዢዎቹን እንዲቈጣጠሩ ዳንኤልንና ሌሎችን ሁለት ሰዎች መረጠ። ዳንኤል ባለው ልዩ የሥራ ችሎታ ከሌሎቹ አገረ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች በልጦ መገኘቱን በተግባር አስመሰከረ፤ ስለዚህ ንጉሡ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሊሾመው አሰበ። ከዚህ በኋላ ሌሎቹ አገረ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች በዳንኤልና በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ ላይ ክስ ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ወንጀል ለማግኘት ፈለጉ፤ ነገር ግን ዳንኤል እጅግ ጠንቃቃና ታማኝ ስለ ነበር ምንም ዐይነት ስሕተት ወይም በደል ሊያገኙበት አልቻሉም። ስለዚህም እርስ በርሳቸው “ከአምላኩ ሕግ በቀር ዳንኤልን የምንከስበት ምንም ዐይነት በደል ማግኘት አልቻልንም” ተባባሉ። ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹና ባለሥልጣኖቹ በማደም ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ! አንተ ለዘለዓለም ኑር! እኛ በመንግሥትህ አስተዳደር ሥራ ላይ የተመደብን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፥ ዐቃብያነ ሕግ፥ እንደራሴዎች፥ አማካሪዎችና አገረ ገዢዎች የተስማማንበት አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም ከአሁን ጀምሮ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው ጸሎት እንዳይደረግ ዐዋጅ እንድታስነግር ነው፤ ይህንንም ዐዋጅ የሚተላለፍ ቢኖር በአንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል እዘዝ። እንግዲህ ንጉሥ ሆይ! ይህ ዐዋጅ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ እንዲሆን ፈርምበት።” በዚህም ዐይነት ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁን በፊርማ አጸና። ዳንኤል ዐዋጁ ተፈርሞበት እንደ ጸና ቢያውቅም እንኳ ወደሚኖርበት ሰገነት ወጣ፤ የሚኖርበትም ሰገነት በኢየሩሳሌም ትይዩ የተከፈቱ መስኮቶች ነበሩት፤ ከዚህ በፊት ያደርገው እንደ ነበረም በጒልበቱ በመንበርከክ አምላኩን እያመሰገነ በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልይ ነበር። እነዚህም ዐድመኞች በአንድነት ሄደው፥ ዳንኤል ወደ ፈጣሪው ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ሁሉም በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው የወጣውን ዐዋጅ በመጣሱ ዳንኤልን እንዲህ ብለው ከሰሱት፦ “ንጉሥ ሆይ፥ እስከ ሠላሳ ቀን ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው የሚጸልይ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ ፈርመህበት አልነበረምን?” ንጉሡም “አዎ፥ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ ዐዋጅ ወጥቶአል” አለ። እነርሱም “እንግዲያውስ ንጉሥ ሆይ! ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል አንተን አያከብርህም፤ ፈርመህበት የወጣውንም ዐዋጅ በመጣስ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት።