ትንቢተ ዳንኤል 2:31-45

ትንቢተ ዳንኤል 2:31-45 አማ05

“ንጉሥ ሆይ! እጅግ የሚያንጸባርቅና ብልጭልጭታው ለማየት የሚያስፈራ ታላቅ ምስል በፊትህ ቆሞ አየህ። የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፥ ደረቱና እጆቹ ከብር፥ ሆዱና ጭኖቹ ከነሐስ፤ ቅልጥሞቹ ከብረት፥ እግሮቹ እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። አንተ ምስሉን ስትመለከት ሳለ ታላቅ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ በተሠሩት በምስሉ እግሮች ላይ ወድቆ ሰባበራቸው። ብረቱ፥ ሸክላው፥ ነሐሱ፥ ብሩና ወርቁ ሁሉ ወዲያውኑ ተንከታክቶ በበጋ ወራት በአውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅ ሆነ፤ ምንም ሳያስቀር ነፋስ ጠራርጎ ወሰደው፤ በምስሉ ላይ የወደቀው ድንጋይ ግን ምድርን ሁሉ እስኪሞላ ድረስ ከፍ ከፍ ብሎ ታላቅ ተራራ ሆነ። “እነሆ፥ ሕልሙ ይህ ነው፤ ትርጒሙም እንደሚከተለው ነው፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ከሁሉ የምትበልጥ ንጉሠ ነገሥት ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኀይልን፤ ሥልጣንና ክብርን ሰጥቶሃል። በምድር ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎሃል፤ በሰው፥ በእንስሶችና በወፎች ላይ ሥልጣን ሰጥቶሃል፤ ስለዚህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። ከአንተ በኋላ በገናናነቱ የአንተን መንግሥት የሚያኽል አነስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ከእርሱም ቀጥሎ ዓለምን ሁሉ የሚገዛ በነሐስ የሚመሰል መንግሥት በሦስተኛ ደረጃ ይነሣል። እንደገናም ሁሉን ነገር የሚሰባብርና የሚያንከታክት እንደ ብረት የጠነከረ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ነገር ሰባብሮ እንደሚያደቅ፥ እርሱም ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቃል። እግሮቹና የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ መሆኑን አይተሃል፤ ይህም የሚያመለክተው ያ መንግሥት የተከፋፈለ መሆኑን ነው፤ ብረት ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ ያ መንግሥት በከፊል እንደ ብረት የጠነከረ ይሆናል። የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ብረት፥ እኩሌታው ሸክላ እንደ ሆነ እንዲሁም ያም መንግሥት በከፊል ብርቱ፥ በከፊል ደካማ ይሆናል። ብረቱ ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ የእነዚያ የሁለት መንግሥታት ሕዝቦች እርስ በርሳቸው በመጋባት ይደባለቃሉ፤ ሆኖም ብረት ከሸክላ መዋሐድ እንደማይችል እነርሱም አንድ መሆን አይችሉም፤ በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ግዛቱም በሌላ ሕዝብ የማይደፈር መንግሥትን ይመሠርታል፤ ይህ መንግሥት ሌሎችን መንግሥታት እስከ መጨረሻው ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ላይ ተፈንቅሎ በመውረድ ከብረት፥ ከነሐስ፥ ከሸክላ፥ ከብርና ከወርቅ የተሠራውን ምስል ያደቀቀውም ድንጋይ፥ ያ መንግሥት ነው፤ በዚህም ታላቁ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ አሳይቶሃል፤ እነሆ፥ ሕልሙ እውነት ነው፤ አስተማማኝ ትርጒሙም ይኸው ነው።”