የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዳንኤል 2:1-45

ትንቢተ ዳንኤል 2:1-45 አማ05

ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም አየ፤ በጣምም ስለ ተጨነቀ እንቅልፍ አጣ። ስለዚህ ወደ እርሱ መጥተው ያየውን ሕልም ይነግሩት ዘንድ ጠንቋዮች፥ አስማተኞች፥ መተተኞችና የከለዳውያን ኮከብ ቈጣሪዎች እንዲጠሩ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነርሱም መጥተው በፊቱ ቆሙ፤ ንጉሡም “ሕልም አይቼ ስለ ነበር ያ ሕልም ምን እንደ ሆነ እስካውቀው ድረስ እጅግ ተጨንቄአለሁ” አላቸው። እነርሱም “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር! ሕልምህ ምን እንደ ሆነ ንገረንና ትርጒሙን እናስረዳሃለን” ሲሉ በሶርያ ቋንቋ መለሱለት። ንጉሡም እንዲህ አላቸው፦ “መጀመሪያ ሕልሜን፥ ቀጥሎም ትርጒሙን ንገሩኝ፤ አለበለዚያ ግን እጅና እግራችሁ እንዲቈራረጥና ቤታችሁ የፍርስራሽ ክምር እንዲሆን ወስኛለሁ። ሕልሙን ከነትርጒሙ ልትነግሩኝ ብትችሉ ግን ሽልማትና ስጦታ ከታላቅ ክብር ጋር እንድታገኙ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ ሕልሙን ከነትርጒሙ ንገሩኝ።” እነርሱም እንደገና “ንጉሥ ሆይ! ሕልምህ ምን እንደ ሆነ ለእኛ ለአገልጋዮችህ ንገረንና እኛም ትርጒሙን እንንገርህ” ሲሉ መለሱለት። ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ የወሰንኩትን ጥብቅ ውሳኔ ስላወቃችሁ የእናንተ ዕቅድ ነገሩን ለማዘግየት መሆኑን ተረድቼአለሁ፤ ሕልሙን ልትነግሩኝ ባትችሉ ለሁላችሁም አንድ ዐይነት ቅጣት ተዘጋጅቶአል፤ ሁኔታዎች የሚለወጡ መስሎአችሁ የሐሰትና የተንኰል ቃል በመናገር ጊዜ ማራዘም ፈልጋችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ብትነግሩኝ ፍቹም እንደማያስቸግራችሁ ዐውቃለሁ።” የከለዳውያን ኮከብ ቈጣሪዎቹም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “ንጉሥ ሆይ! አንተ ለማወቅ የምትፈልገውን ነገር ሊነግርህ የሚችል ሰው በዓለም ላይ አይገኝም፤ አንድ ንጉሥ የቱንም ያኽል ታላቅና ብርቱ ቢሆን ይህን የመሰለ ጥያቄ ለጠንቋዮች፥ ለአስማተኞችና ለኮከብ ቈጣሪዎች አቅርቦ አያውቅም። ንጉሥ ሆይ! አንተ ለምታቀርበው ከባድ ጥያቄ ከአማልክት በቀር መልስ መስጠት የሚችል የለም፤ አማልክት ደግሞ በሰው መካከል የሚኖሩ አይደሉም።” በዚህን ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቈጥቶ በባቢሎን የሚኖሩ ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉ አዘዘ። ጠቢባን እንዲገደሉ በወጣው ትእዛዝ መሠረት ዳንኤልንና ጓደኞቹንም አብረው ለመግደል ፈለጉአቸው። ውሳኔውን በሥራ ላይ እንዲያውል የተመደበው አርዮክ የተባለው የንጉሡ የክብር ዘብ አዛዥ ነበር፤ ስለዚህ ዳንኤል ወደ እርሱ ሄደና በዘዴ አነጋገር፦ “ንጉሡ ይህን ከባድ ውሳኔ ያስተላለፈው እንዴት ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ አርዮክም ጉዳዩን ለዳንኤል ገልጦ አስረዳው። ዳንኤልም ወዲያውኑ ገብቶ ሕልሙን ለመተርጐም ጥቂት ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ለመነ። ከዚህ በኋላ ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደና የሆነውን ነገር ለጓደኞቹ ለሐናንያ፥ ለሚሳኤልና ለዐዛርያ ነገራቸው። እነርሱም ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይገደሉ የሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲያደርግላቸውና ምሥጢሩንም እንዲገልጥላቸው ይለምኑት ዘንድ አሳሰባቸው። በዚያኑ ሌሊት ምሥጢሩ ለዳንኤል በራእይ ተገለጠለት፤ ስለዚህ የሰማይን አምላክ እንዲህ ሲል አመሰገነ፦ “ጥበብም ኀይልም የእርሱ ስለ ሆነ እግዚአብሔር ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን! እርሱ ጊዜያትንና ወራትን ያፈራርቃል፤ ነገሥታትን ወደ ዙፋን ያወጣል፤ ከዙፋንም ያወርዳል፤ ጥበብን ለጠቢባን፥ ዕውቀትንም ለአስተዋዮች የሚሰጥ እርሱ ነው። እርሱ ጥልቅ የሆነውን ምሥጢርና የተሰወረውን ነገር ይገልጣል፤ በእርሱ ዘንድ ሁልጊዜ ብርሃን ስላለ፥ በጨለማ የተሰወረውን ያውቃል። የቀድሞ አባቶቼ አምላክ ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤ ከፍ ከፍም አደርግሃለሁ፤ አንተ ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛል፤ ጸሎታችንንም ሰምተህ የንጉሡን ሕልም ገልጠህልናል።” ከዚህ በኋላ ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን እንዲገድል ከንጉሡ ትእዛዝ ወደተሰጠው ወደ አርዮክ ሄደና “የባቢሎንን ጠቢባን አትግደል፤ ይልቅስ ወደ ንጉሡ አቅርበኝና የሕልሙን ትርጒም ልንገረው” አለው። አርዮክ ወዲያውኑ ዳንኤልን ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር ፊት አቀረበውና፥ “ንጉሥ ሆይ! የሕልምህን ትርጒም የሚነግርህ ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አንድ ሰው አግኝቼአለሁ” ሲል ለንጉሡ ተናገረ። ንጉሡም ብልጣሶር ተብሎ የሚጠራውን ዳንኤልን “ያየሁትን ሕልም ከነትርጒሙ ልትነግረኝ ትችላለህን?” ሲል ጠየቀው። ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! አንተ የጠየቅኸውን ምሥጢር ጠቢባንም ሆኑ አስማተኞች፤ ጠንቋዮችም ሆኑ መተተኞች ሊነግሩህ አይችሉም። ነገር ግን ምሥጢርን ሁሉ የሚገልጥ አንድ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱ ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ ለአንተ ገልጦልሃል፤ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ያየኸው ሕልምና በአእምሮህ የነበረው ራእይ የሚከተለው ነው። “ንጉሥ ሆይ! አንተ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር ታሰላስል ነበር፤ ስለዚህ ምሥጢርን የሚገልጥ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስታወቀህ። ይህም ምሥጢር ለእኔ የተገለጠልኝ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ጥበበኛ ስለ ሆንኩ አይደለም፤ ነገር ግን አንተ የሕልሙን ትርጒም እንድታውቅና በአእምሮህም ውስጥ የተመላለሰውን ሐሳብ መረዳት እንድትችል ነው። “ንጉሥ ሆይ! እጅግ የሚያንጸባርቅና ብልጭልጭታው ለማየት የሚያስፈራ ታላቅ ምስል በፊትህ ቆሞ አየህ። የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፥ ደረቱና እጆቹ ከብር፥ ሆዱና ጭኖቹ ከነሐስ፤ ቅልጥሞቹ ከብረት፥ እግሮቹ እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። አንተ ምስሉን ስትመለከት ሳለ ታላቅ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ በተሠሩት በምስሉ እግሮች ላይ ወድቆ ሰባበራቸው። ብረቱ፥ ሸክላው፥ ነሐሱ፥ ብሩና ወርቁ ሁሉ ወዲያውኑ ተንከታክቶ በበጋ ወራት በአውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅ ሆነ፤ ምንም ሳያስቀር ነፋስ ጠራርጎ ወሰደው፤ በምስሉ ላይ የወደቀው ድንጋይ ግን ምድርን ሁሉ እስኪሞላ ድረስ ከፍ ከፍ ብሎ ታላቅ ተራራ ሆነ። “እነሆ፥ ሕልሙ ይህ ነው፤ ትርጒሙም እንደሚከተለው ነው፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ከሁሉ የምትበልጥ ንጉሠ ነገሥት ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኀይልን፤ ሥልጣንና ክብርን ሰጥቶሃል። በምድር ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎሃል፤ በሰው፥ በእንስሶችና በወፎች ላይ ሥልጣን ሰጥቶሃል፤ ስለዚህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። ከአንተ በኋላ በገናናነቱ የአንተን መንግሥት የሚያኽል አነስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ከእርሱም ቀጥሎ ዓለምን ሁሉ የሚገዛ በነሐስ የሚመሰል መንግሥት በሦስተኛ ደረጃ ይነሣል። እንደገናም ሁሉን ነገር የሚሰባብርና የሚያንከታክት እንደ ብረት የጠነከረ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ነገር ሰባብሮ እንደሚያደቅ፥ እርሱም ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቃል። እግሮቹና የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ከብረት፥ እኩሌታው ከሸክላ መሆኑን አይተሃል፤ ይህም የሚያመለክተው ያ መንግሥት የተከፋፈለ መሆኑን ነው፤ ብረት ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ ያ መንግሥት በከፊል እንደ ብረት የጠነከረ ይሆናል። የእግሮቹ ጣቶች አሠራር እኩሌታው ብረት፥ እኩሌታው ሸክላ እንደ ሆነ እንዲሁም ያም መንግሥት በከፊል ብርቱ፥ በከፊል ደካማ ይሆናል። ብረቱ ከሸክላ ጋር ተደባልቆ እንዳየህ የእነዚያ የሁለት መንግሥታት ሕዝቦች እርስ በርሳቸው በመጋባት ይደባለቃሉ፤ ሆኖም ብረት ከሸክላ መዋሐድ እንደማይችል እነርሱም አንድ መሆን አይችሉም፤ በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ግዛቱም በሌላ ሕዝብ የማይደፈር መንግሥትን ይመሠርታል፤ ይህ መንግሥት ሌሎችን መንግሥታት እስከ መጨረሻው ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ላይ ተፈንቅሎ በመውረድ ከብረት፥ ከነሐስ፥ ከሸክላ፥ ከብርና ከወርቅ የተሠራውን ምስል ያደቀቀውም ድንጋይ፥ ያ መንግሥት ነው፤ በዚህም ታላቁ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ አሳይቶሃል፤ እነሆ፥ ሕልሙ እውነት ነው፤ አስተማማኝ ትርጒሙም ይኸው ነው።”