የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 2:1-45

ዳንኤል 2:1-45 NASV

ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም ዐለመ፤ መንፈሱ ታወከ፤ እንቅልፍም ከርሱ ራቀ። ያለመውንም ሕልም እንዲነግሩት ንጉሡ ጠንቋዮችን፣ አስማተኞችን፣ መተተኞችንና ኮከብ ቈጣሪዎችን እንዲጠሩ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በፊቱ ቆሙ፤ ንጉሡም፣ “አንድ ሕልም ዐለምሁ፤ ሕልሙም ምን እንደ ሆነ ለማወቅ መንፈሴ ተጨንቋል” አላቸው። ከዚያም ኮከብ ቈጣሪዎቹ ለንጉሡ በአራማይክ ቋንቋ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ሕልምህን ለአገልጋዮችህ ንገረን፤ እኛም እንፈታልሃለን” አሉት። ንጉሡም ለኮከብ ቈጣሪዎቹ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕልሙንና ትርጕሙን ባትነግሩኝ አካላችሁ እንዲቈራረጥና ቤቶቻችሁም የፍርስራሽ ክምር እንዲሆኑ ወስኛለሁ፤ ነገር ግን ሕልሙንና ትርጕሙን ብትነግሩኝ፣ ስጦታና ሽልማት፣ ታላቅ ክብርም ከእኔ ትቀበላላችሁ፤ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጕሙንም አሳውቁኝ።” እነርሱም እንደ ገና፣ “ንጉሥ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገረን፤ እኛም እንተረጕመዋለን” ብለው መለሱ። ንጉሡም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ምን ብዬ እንደ ወሰንሁ ስለምታውቁ፣ ጊዜ ለማራዘም እንደምትሞክሩ ተረድቻለሁ፤ ሕልሙን ባትነግሩኝ፣ አንድ ቅጣት ይጠብቃችኋል፤ ሁኔታው ይለወጣል ብላችሁ በማሰብ የሚያሳስቱ ነገሮችንና ክፉ ሐሳቦችን ልትነግሩኝ አሲራችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጕሙንም ልትነግሩኝ እንደምትችሉ በዚህ ዐውቃለሁ።” ኮከብ ቈጣሪዎቹም ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ንጉሡ የጠየቀውን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ሰው በምድር ላይ አይገኝም! ማንም ንጉሥ ምንም ያህል ታላቅና ኀያል ቢሆን፣ እንዲህ ዐይነት ነገር ማንኛውንም ጠንቋይ፣ አስማተኛ ወይም ኮከብ ቈጣሪን ጠይቆ አያውቅም። ንጉሡ የሚጠይቀው እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው፤ በሰዎች መካከል ከማይኖሩት ከአማልክት በቀር ለንጉሡ የሚገልጽለት የለም።” ይህም ንጉሡን እጅግ አበሳጨው፤ አስቈጣውም፤ በባቢሎን ያሉ ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም አዘዘ፤ ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም ዐዋጅ ወጣ፤ ዳንኤልንና ጓደኞቹን ፈልገው እንዲገድሉ ሰዎች ተላኩ። የንጉሡ ዘበኞች አለቃ አርዮክ፣ የባቢሎንን ጠቢባን ለመግደል በመጣ ጊዜ፣ ዳንኤል በጥበብና በዘዴ አነጋገረው። የንጉሡን መኰንን፣ “ንጉሡ እንዲህ ዐይነት ከባድ ዐዋጅ ያወጣው ስለ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው፤ አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል ገለጠለት። በዚህ ጊዜ፣ ዳንኤልም ገብቶ ሕልሙን ይተረጕምለት ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው። ከዚህ በኋላ ዳንኤል ወደ ቤቱ ተመልሶ ለጓደኞቹ ለአናንያ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያ ነገሩን ገለጠላቸው። እርሱና ጓደኞቹ ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋራ እንዳይገደሉ፣ የሰማይ አምላክ ምሕረት ያደርግላቸውና ምስጢሩንም ይገልጥላቸው ዘንድ እንዲጸልዩ አሳሰባቸው። ለዳንኤልም ምስጢሩ በሌሊት በራእይ ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፤ “ጥበብና ኀይል የርሱ ነውና፣ የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ። ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፣ ደግሞም ያወርዳቸዋል፤ ጥበብን ለጠቢባን፣ ዕውቀትንም ለሚያስተውሉ ይሰጣል። የጠለቀውንና የተሰወረውን ነገር ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፤ ብርሃንም ከርሱ ጋራ ይኖራል። የአባቶቼ አምላክ ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ፤ አከብርሃለሁም፤ ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛልና፤ ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤ የንጉሡን ሕልም አሳውቀኸናል።” ዳንኤልም የባቢሎንን ጠቢባን እንዲገድል ንጉሡ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ሄዶ፣ “የባቢሎንን ጠቢባን አትግደል፤ ወደ ንጉሡ ውሰደኝ፤ እኔም ሕልሙን እተረጕምለታለሁ” አለው። አርዮክም ዳንኤልን ወዲያውኑ ወደ ንጉሡ በመውሰድ፣ “ሕልሙንና ትርጕሙን ለንጉሡ መግለጥ የሚችል ሰው ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አግኝቻለሁ” አለው። ንጉሡም ብልጣሶር የተባለውን ዳንኤልን፣ “ያየሁትን ሕልምና ትርጕሙን ልትነግረኝ ትችላለህን?” አለው። ዳንኤልም እንዲህ አለ፤ “አንድም ጠቢብ፣ አስማተኛ፣ ጠንቋይም ሆነ ቃላተኛ ንጉሡ የጠየቀውን ምስጢር መግለጥ የሚችል የለም፤ ነገር ግን ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም በሚመጡት ዘመናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነፆር ገልጧል፤ በዐልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ በአእምሮህ የነበረው ሕልምና ራእይ ይህ ነው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ተኝተህ ሳለ፣ አእምሮህ ወደ ፊት ሊሆን ስላለው ነገር ያሰላስል ነበር፤ ምስጢርን ገላጭ የሆነውም ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር አሳየህ። ይህ ምስጢር ለእኔ የተገለጠው፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ታላቅ ጥበብ ስላለኝ አይደለም፤ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ትርጕሙን እንድታውቅና በአእምሮህ ታሰላስለው የነበረው ነገር ምን እንደ ሆነ ትረዳ ዘንድ ነው። “ንጉሥ ሆይ፤ በፊት ለፊትህ ግዙፍ የሆነ፣ የሚያብረቀርቅና የሚያስፈራ ታላቅ ምስል ቆሞ አየህ፤ የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከናስ የተሠሩ ነበሩ፤ ቅልጥሞቹም ከብረት፣ እግሮቹም ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉም ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም። ወዲያውኑም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው፤ ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ። “ሕልሙ ይህ ነበር፤ አሁን ትርጕሙን ለንጉሥ እንናገራለን። ንጉሥ ሆይ፤ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል፤ የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል፤ እንግዲህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። “ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ቀጥሎም በናስ የተመሰለው ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ መላውን ምድርም ይገዛል። በመጨረሻም ሁሉን ነገር እንደሚቀጠቅጥና እንደሚሰብር ብረት ብርቱ የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ሰባብሮ እንደሚያደቅ ከርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቅቃቸዋል። እግሮቹና ጣቶቹ ከፊል ብረትና ከፊል ሸክላ ሆነው እንዳየህ፣ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ነገር ግን ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ በከፊል የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል። የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት ከፊሉ ሸክላ እንደ ሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊሉ ብርቱ በከፊሉ ደካማ ይሆናል። ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ ብረትና ሸክላ እንደማይዋሃድ ሁሉ ሕዝቡም በአንድነት አይኖሩም። “በእነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ የወረደውና ብረቱን፣ ናሱን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ያደቀቀው ድንጋይ ራእይ ትርጓሜ ይህ ነው፤ “ታላቁ አምላክ ወደ ፊት የሚሆነውን ለንጉሡ አሳይቶታል፤ ሕልሙ እውነት ነው፤ ትርጓሜውም የታመነ ነው።”