እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ፥ በዓላትን ወይም የወር መባቻን፥ ወይም ሰንበትን በማክበር ምክንያት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሁሉ ወደፊት ይመጡ ለነበሩት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸው፤ እውነቱ የሚገኘው ግን በክርስቶስ ነው። በአጉል ትሕትናና መላእክትን በማምለክ የሚመካ ማንም ሰው ያለ ዋጋ እንዳያስቀራችሁ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ዐይነቱ ሰው ስለሚያየው ራእይ እየተመጻደቀ ከንቱና ሥጋዊ በሆነ አስተሳሰብ ይታበያል። እንዲህ ያለ ሰው ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ አካልን በሙሉ በመገጣጠሚያና በጅማት አያይዞ የሚመግበው ራስ ነው። እግዚአብሔር ለአካል ሙሉ ዕድገት የሚሰጠውም በዚህ ዐይነት ነው። ከክርስቶስ ጋር ሞታችሁ ከዚህ ዓለም መሠረታዊ ሥርዓቶች ፈጽማችሁ የተለያችሁ ከሆናችሁ ታዲያ፥ አሁን ከዓለም እንዳልተለያችሁ ዐይነት ሆናችሁ ስለምን እንደዚህ ላሉት ትእዛዞች ትገዛላችሁ፤ ትእዛዞቹም “አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ” የሚሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ በሰው ሠራሽ ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ ሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ ለመጥፋት የተወሰኑ ናቸው። እነዚህ ትእዛዞች ከገዛ ፈቃድ በመነጨ አምልኮና በአጉል ትሕትና፥ ሰውነትንም በማጐሳቈል ላይ ስለሚያተኲሩ ጥበብ ያላቸው ይመስሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ሥጋዊ ስሜትን በመቈጣጠር ረገድ ዋጋቢሶች ናቸው።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2:16-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች