ቈላስይስ 2:16-23

ቈላስይስ 2:16-23 NASV

እንግዲህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ ወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ነገር ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ዐጕል ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ የሚወድድ ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየው ራእይ ከመጠን በላይ ራሱን እየካበ በሥጋዊ አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል፤ ይህ ሰው፣ አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ እየተጋጠመ ምግብንም እየተቀበለ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ከሚያድግበት ራስ ከሆነው ጋራ ግንኙነት የለውም። ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋራ ከሞታችሁ፣ ታዲያ በዚህ ዓለም እንደሚኖር ለምን ትገዙላቸዋላችሁ? “አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት ዐይነት፣ እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።