የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:3-12

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:3-12 አማ05

ለእናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ዘወትር እናመሰግናለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን እምነትና ስለ ምእመናን ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ሰምተናል። የእውነት ቃል የሆነው ወንጌል በመጀመሪያ ወደ እናንተ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ያለውን ተስፋ ሰምታችኋል፤ ስለዚህ እምነታችሁና ፍቅራችሁ የተመሠረተው በሰማይ ተዘጋጅቶ በሚቈያችሁ በዚህ ተስፋ ላይ ነው። እናንተ ወንጌልን ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርንም ጸጋ እውነተኛነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ ይህ ወንጌል በእናንተ መካከል እንደሆነው በመላው ዓለም በማፍራትና በማደግ ላይ ነው። ይህንንም በእኛ ምትክ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነውና ከእኛም ጋር አብሮን የሚሠራው የተወደደው ኤጳፍራ ነግሮአችኋል። እንዲሁም እርሱ በእግዚአብሔር መንፈስ እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን ነግሮናል። ስለዚህ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እናንተ በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምትገነዘቡበት ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራችሁ ለእናንተ ከመጸለይና እግዚአብሔርን ከመለመን አላቋረጥንም። እንዲሁም ለጌታ ተገቢ በሆነ መንገድ በመኖር እርሱን በፍጹም እንድታስደስቱ ማናቸውንም መልካም ሥራ በመሥራት ፍሬ እንድታፈሩና እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ እንድትሄዱ እንጸልያለን። ጌታ በገናናው ኀይሉ ብርታቱን ሁሉ ይስጣችሁ፤ በትዕግሥትም ሁሉን ነገር ለመቻል በደስታ የተዘጋጃችሁ ለመሆን ያብቃችሁ፤ ደግሞም በብርሃን መንግሥት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ርስት እንድትካፈሉ ያበቃችሁን እግዚአብሔር አብን በደስታ አመስግኑት።