የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1

1
1በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፥
2በቈላስይስ ለሚኖሩ፥ በክርስቶስ ቅዱሳንና ታማኞች ለሆኑ አማኞች፥
ከእግዚአብሔር ከአባታችን ጸጋና ሰላም ይሁንላችሁ።
የጳውሎስ ምስጋና ለቆላስይስ ሰዎች
3ለእናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ዘወትር እናመሰግናለን። 4በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን እምነትና ስለ ምእመናን ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ሰምተናል። 5የእውነት ቃል የሆነው ወንጌል በመጀመሪያ ወደ እናንተ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ያለውን ተስፋ ሰምታችኋል፤ ስለዚህ እምነታችሁና ፍቅራችሁ የተመሠረተው በሰማይ ተዘጋጅቶ በሚቈያችሁ በዚህ ተስፋ ላይ ነው። 6እናንተ ወንጌልን ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርንም ጸጋ እውነተኛነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ ይህ ወንጌል በእናንተ መካከል እንደሆነው በመላው ዓለም በማፍራትና በማደግ ላይ ነው። 7ይህንንም በእኛ ምትክ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነውና ከእኛም ጋር አብሮን የሚሠራው የተወደደው ኤጳፍራ ነግሮአችኋል። #1፥7 በእኛ፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “በእናንተ” ይላሉ። #ቆላ. 4፥12። 8እንዲሁም እርሱ በእግዚአብሔር መንፈስ እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን ነግሮናል።
9ስለዚህ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እናንተ በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምትገነዘቡበት ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራችሁ ለእናንተ ከመጸለይና እግዚአብሔርን ከመለመን አላቋረጥንም። 10እንዲሁም ለጌታ ተገቢ በሆነ መንገድ በመኖር እርሱን በፍጹም እንድታስደስቱ ማናቸውንም መልካም ሥራ በመሥራት ፍሬ እንድታፈሩና እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ እንድትሄዱ እንጸልያለን። 11ጌታ በገናናው ኀይሉ ብርታቱን ሁሉ ይስጣችሁ፤ በትዕግሥትም ሁሉን ነገር ለመቻል በደስታ የተዘጋጃችሁ ለመሆን ያብቃችሁ፤ 12ደግሞም በብርሃን መንግሥት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ርስት እንድትካፈሉ ያበቃችሁን እግዚአብሔር አብን በደስታ አመስግኑት። 13እርሱ ከጨለማ ኀይል አድኖ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥት እንድንገባ አድርጎናል። 14በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አግኝተናል።
የክርስቶስ ልዕልና #ኤፌ. 1፥7
15ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳሌ ነው። እርሱ ከፍጥረት ሁሉ በላይ ታላቅና በኲር ነው። 16በሰማይና በምድር ያሉት፥ የሚታዩትና የማይታዩት፥ የሰማይ ኀይሎችና ገዢዎች፥ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው። 17እርሱ ከሁሉ ነገር በፊት ነበረ፤ ሁሉም ነገር ተያይዞ የቆመው በእርሱ ነው። 18እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር ቀዳሚ እንዲሆን፤ ከሞት በመነሣትም ፊተኛና መጀመሪያ ነው። #ኤፌ. 1፥22-23። 19ይህም የሆነው የመለኮት ሙላት በልጁ እንዲኖር የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ስለ ሆነ ነው። 20በእርሱም አማካይነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ፤ በመስቀል ላይ በፈሰሰው በልጁ ደምም ሰላምን አደረገ። #ኤፌ. 2፥16።
21ቀድሞ ከእግዚአብሔር ርቃችሁ ትኖሩ ነበር፤ በሐሳባችሁና በክፉ ሥራችሁም ምክንያት ጠላቶቹ ነበራችሁ። 22አሁን ግን ቅዱሳንና ንጹሓን፥ ነቀፋም የሌለባችሁ አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ፥ ልጁ በሥጋ በመሞቱ ምክንያት እግዚአብሔር ከራሱ ጋር አስታረቃችሁ። 23ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በወንጌሉ ከተገኘው ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት ጸንታችሁ ስትኖሩ ብቻ ነው፤ ይህም ወንጌል እናንተ የሰማችሁትና በዓለም ላይ ላሉት ሰዎች ሁሉ የተሰበከ ነው፤ እኔ ጳውሎስም አገልጋይ የሆንኩት ለዚሁ ወንጌል ነው።
የጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት
24አሁን ስለ እናንተ በምቀበለው መከራ ደስ ይለኛል፤ አካሉ ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያንም ከክርስቶስ መከራ ከመካፈል የጐደለብኝን በሥጋዬ አሟላለሁ። 25የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ በሙሉ እገልጥ ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ኀላፊነት መሠረት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኜአለሁ። 26ይህም የእግዚአብሔር ቃል ባለፉት ዘመናት ከሰው ልጆች ተሰውሮ የቈየውና አሁን ግን እግዚአብሔር ለሚያምኑት ሁሉ የገለጠው ምሥጢር ነው። 27እግዚአብሔርም ለቅዱሳኑ ሊገልጥላቸው የፈቀደው ያለውን የዚህን ምሥጢር የክብር ብልጽግና በእናንተ በአሕዛብ መካከል ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ነው። ይህም ምሥጢር በተስፋ የምንጠባበቀው ክብር የሚገኝበት ክርስቶስ በእናንተ መካከል መሆኑ ነው። 28እያንዳንዱ ሰው በክርስቶስ ብቁ ሰው እንዲሆን አድርገን ለማቅረብ ለሰው ሁሉ ጥበብን ሁሉ በማስተማርና በመምከር ስለ ክርስቶስ እንሰብካለን። 29እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ በእኔ ውስጥ ስለሚሠራ በዚህ ኀይል አማካይነት ይህ ዓላማ እንዲፈጸም በብርቱ እየታገልኩ እደክማለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ