የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ቈላስይስ 1:3-12

ቈላስይስ 1:3-12 NASV

ስለ እናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተናል፤ ይህም የሆነው በሰማይ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠላችሁ ተስፋ የተነሣ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ በወንጌል የእውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ፤ ይህም ወደ እናንተ ደርሷል። ይህንም ወንጌል ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ በዓለም ዙሪያ እየሠራ እንዳለ ሁሉ በእናንተም ዘንድ ፍሬ እያፈራና እያደገ ነው። ይህንም ስለ እኛ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነው፣ ዐብሮንም በአገልግሎት የተጠመደው ተወዳጁ ኤጳፍራ አስተማራችሁ፤ ደግሞም በመንፈስ ስላላችሁ ፍቅር ነገረን። ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤ የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣ በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑ ነው።