በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፥ በቈላስይስ ለሚኖሩ፥ በክርስቶስ ቅዱሳንና ታማኞች ለሆኑ አማኞች፥ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ጸጋና ሰላም ይሁንላችሁ። ለእናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ዘወትር እናመሰግናለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን እምነትና ስለ ምእመናን ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ሰምተናል። የእውነት ቃል የሆነው ወንጌል በመጀመሪያ ወደ እናንተ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ያለውን ተስፋ ሰምታችኋል፤ ስለዚህ እምነታችሁና ፍቅራችሁ የተመሠረተው በሰማይ ተዘጋጅቶ በሚቈያችሁ በዚህ ተስፋ ላይ ነው። እናንተ ወንጌልን ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርንም ጸጋ እውነተኛነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ ይህ ወንጌል በእናንተ መካከል እንደሆነው በመላው ዓለም በማፍራትና በማደግ ላይ ነው። ይህንንም በእኛ ምትክ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነውና ከእኛም ጋር አብሮን የሚሠራው የተወደደው ኤጳፍራ ነግሮአችኋል። እንዲሁም እርሱ በእግዚአብሔር መንፈስ እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን ነግሮናል። ስለዚህ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እናንተ በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምትገነዘቡበት ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራችሁ ለእናንተ ከመጸለይና እግዚአብሔርን ከመለመን አላቋረጥንም። እንዲሁም ለጌታ ተገቢ በሆነ መንገድ በመኖር እርሱን በፍጹም እንድታስደስቱ ማናቸውንም መልካም ሥራ በመሥራት ፍሬ እንድታፈሩና እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ እንድትሄዱ እንጸልያለን። ጌታ በገናናው ኀይሉ ብርታቱን ሁሉ ይስጣችሁ፤ በትዕግሥትም ሁሉን ነገር ለመቻል በደስታ የተዘጋጃችሁ ለመሆን ያብቃችሁ፤ ደግሞም በብርሃን መንግሥት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ርስት እንድትካፈሉ ያበቃችሁን እግዚአብሔር አብን በደስታ አመስግኑት። እርሱ ከጨለማ ኀይል አድኖ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥት እንድንገባ አድርጎናል። በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አግኝተናል። ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳሌ ነው። እርሱ ከፍጥረት ሁሉ በላይ ታላቅና በኲር ነው። በሰማይና በምድር ያሉት፥ የሚታዩትና የማይታዩት፥ የሰማይ ኀይሎችና ገዢዎች፥ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው። እርሱ ከሁሉ ነገር በፊት ነበረ፤ ሁሉም ነገር ተያይዞ የቆመው በእርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር ቀዳሚ እንዲሆን፤ ከሞት በመነሣትም ፊተኛና መጀመሪያ ነው። ይህም የሆነው የመለኮት ሙላት በልጁ እንዲኖር የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ስለ ሆነ ነው። በእርሱም አማካይነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ፤ በመስቀል ላይ በፈሰሰው በልጁ ደምም ሰላምን አደረገ። ቀድሞ ከእግዚአብሔር ርቃችሁ ትኖሩ ነበር፤ በሐሳባችሁና በክፉ ሥራችሁም ምክንያት ጠላቶቹ ነበራችሁ። አሁን ግን ቅዱሳንና ንጹሓን፥ ነቀፋም የሌለባችሁ አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ፥ ልጁ በሥጋ በመሞቱ ምክንያት እግዚአብሔር ከራሱ ጋር አስታረቃችሁ። ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በወንጌሉ ከተገኘው ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት ጸንታችሁ ስትኖሩ ብቻ ነው፤ ይህም ወንጌል እናንተ የሰማችሁትና በዓለም ላይ ላሉት ሰዎች ሁሉ የተሰበከ ነው፤ እኔ ጳውሎስም አገልጋይ የሆንኩት ለዚሁ ወንጌል ነው። አሁን ስለ እናንተ በምቀበለው መከራ ደስ ይለኛል፤ አካሉ ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያንም ከክርስቶስ መከራ ከመካፈል የጐደለብኝን በሥጋዬ አሟላለሁ። የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ በሙሉ እገልጥ ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ኀላፊነት መሠረት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኜአለሁ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል ባለፉት ዘመናት ከሰው ልጆች ተሰውሮ የቈየውና አሁን ግን እግዚአብሔር ለሚያምኑት ሁሉ የገለጠው ምሥጢር ነው። እግዚአብሔርም ለቅዱሳኑ ሊገልጥላቸው የፈቀደው ያለውን የዚህን ምሥጢር የክብር ብልጽግና በእናንተ በአሕዛብ መካከል ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ነው። ይህም ምሥጢር በተስፋ የምንጠባበቀው ክብር የሚገኝበት ክርስቶስ በእናንተ መካከል መሆኑ ነው። እያንዳንዱ ሰው በክርስቶስ ብቁ ሰው እንዲሆን አድርገን ለማቅረብ ለሰው ሁሉ ጥበብን ሁሉ በማስተማርና በመምከር ስለ ክርስቶስ እንሰብካለን። እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ በእኔ ውስጥ ስለሚሠራ በዚህ ኀይል አማካይነት ይህ ዓላማ እንዲፈጸም በብርቱ እየታገልኩ እደክማለሁ።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:1-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos