የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ከግብጽ ባወጣችሁ፥ በእናንተ በመላው ሕዝብ ላይ እግዚአብሔር የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤ “በዓለም ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የመረጥኩት እናንተን ብቻ ነው፤ በምትሠሩት ኃጢአት ሁሉ የምቀጣችሁ ስለዚህ ነው።” ሁለት ሰዎች አብረው ለመሄድ ካልተቀጣጠሩ በቀር በአንድነት ለመሄድ ይችላሉን? አንበሳ በደን ውስጥ ዐድኖ የሚበላውን ሳያገኝ በከንቱ ያገሣልን? የአንበሳ ደቦልስ አንዳች ነገር ዐድኖ ሳይዝ በሚኖርበት ቦታ ድምፁን ያሰማልን? ወፍ ያለ ማጥመጃ ወጥመድ ውስጥ ገብቶ ይያዛልን? ወጥመድስ አንዳች ነገር ሳይነካው ይፈናጠራልን? ለጦርነት የሚያዘጋጅ መለከት በከተማ ውስጥ ሲነፋ በፍርሃት የማይንቀጠቀጥ ሕዝብ ይኖራልን? እግዚአብሔር ካልፈቀደ በቀር በከተማ ላይ ክፉ ነገር ይመጣልን? ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት አስቀድሞ ሳይገልጥ ምንም ነገር አያደርግም። አንበሳ ሲያገሣ ሰምቶ የማይፈራ ማን አለ? ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ሲገልጥለት ትንቢት የማይናገር ማን አለ? በአሽዶድና በግብጽ በሚገኙ ምሽጎች ለሚኖሩ ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ዐውጁ፦ “በሰማርያ ተራራ ላይ ተሰብሰቡ፤ እዚያ ውስጥም የሚፈጸመውን ግፍና ያለውን ሁከት ተመልከቱ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ ሕዝቦች መልካም ነገር ማድረግን አያውቁም፤ በዐመፅና በግፍ በተወሰደ ንብረት ምሽጋቸውን ይሞላሉ፤ ስለዚህ ጠላት አገራቸውን ይከባል፤ ምሽጎቻቸውንም አፈራርሶ ቤቶቻቸውን ይዘርፋል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሰማርያ የሚኖሩ እስራኤላውያን ከአልጋና ከድንክ አልጋ ቊራጭ ጋር ያመልጣሉ፤ ይኸውም እረኛ ከአንበሳ መንጋጋ ሁለት እግርና የጆሮ ቊራጭ ለማስጣል እንደሚችለው ዐይነት ነው።” የሠራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ይህን ስሙ፤ በያዕቆብ ዘሮች ላይ መስክሩ። ስለ ሠሩት ኃጢአት የእስራኤልን ሕዝብ በምቀጣበት ቀን በቤትኤል የሚገኙትን መሠዊያዎች አፈራርሳለሁ፤ የመሠዊያዎቹም ቀንዶች ተሰባብረው በምድር ላይ ይወድቃሉ። የክረምቱንና የበጋውን ወራት የሚያሳልፉባቸውን ቤቶች ሁሉ እደመስሳለሁ፤ በዝሆን ጥርስ አጊጠው የተሠሩ ቤቶች ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ታላላቅ ቤቶች ሁሉ ይወድማሉ።”
ትንቢተ አሞጽ 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ አሞጽ 3:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos