የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አሞጽ 3:1-15

አሞጽ 3:1-15 NASV

የእስራኤል ልጆች ሆይ፤ እግዚአብሔር በእናንተ ከግብጽ ባወጣሁት ሕዝብ ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤ “ከምድር ወገን ሁሉ፣ እናንተን ብቻ መረጥሁ፤ ስለዚህ ስለ ሠራችሁት ኀጢአት ሁሉ፣ እኔ እቀጣችኋለሁ።” በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ፣ ዐብረው መጓዝ ይችላሉን? አንበሳ የሚበላውን ሳያገኝ፣ በጫካ ውስጥ ይጮኻልን? ምንም ነገርስ ሳይዝ፣ በዋሻው ውስጥ ያገሣልን? ወጥመድ ሳይዘረጋ፣ ወፍ በምድር ላይ ይጠመዳልን? የሚይዘው ነገር ሳይኖርስ፣ ወጥመዱ ከምድር ይፈነጠራልን? የመለከት ድምፅ በከተማ ውስጥ ሲሰማ፣ ሰዎች አይደነግጡምን? ጥፋትስ በከተማ ላይ ቢደርስ፣ ያደረገው እግዚአብሔር አይደለምን? በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምስጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣ ምንም ነገር አያደርግም። አንበሳ አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው? ለአዛጦን ምሽግ፣ ለግብጽም ምሽግ እንዲህ ብላችሁ ዐውጁ፤ “በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፤ በውስጧ ያለውን ታላቅ ሁከት፣ በሕዝቧም መካከል ያለውን ግፍ እዩ።” “ቅሚያንና ዝርፊያን በምሽጋቸው ውስጥ የሚያከማቹ፣ በጎ ነገር ማድረግን አያውቁም፤” ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጠላት ምድሪቱን ይወርራል፤ ምሽጎቻችሁን ያፈርሳል፤ ድንኳኖቻችሁን ይዘርፋል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እረኛ ከአንበሳ መንጋጋ፣ ሁለት የእግር ዐጥንት ወይም የጆሮ ቍራጭ እንደሚያድን፣ እንዲሁም በሰማርያ በዐልጋቸው ጫፍ ላይ፣ በደማስቆም በምንጣፋቸው ላይ የተቀመጡ፣ እስራኤላውያን ይድናሉ።” “ይህን ስሙ፤ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ” ይላል የሰራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር። “እስራኤልን ስለ ኀጢአቷ በምቀጣበት ቀን፣ የቤቴልን መሠዊያዎች አፈርሳለሁ፤ የመሠዊያው ቀንዶች ይቈረጣሉ፤ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። የክረምቱን ቤት፣ ከበጋው ቤት ጋራ እመታለሁ፤ በዝኆን ጥርስ ያጌጡ ቤቶችም ይደመሰሳሉ፤ ታላላቅ አዳራሾችም ይፈርሳሉ፤” ይላል እግዚአብሔር።