ትንቢተ አሞጽ 2:1-16

ትንቢተ አሞጽ 2:1-16 አማ05

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሞአብ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የኤዶምን ንጉሥ ዐፅም ዐመድ እስኪሆን አቃጥለዋል፤ ስለዚህ በሞአብ ምድር እሳት እለቅበታለሁ፤ የቂሪዮትንም ምሽጎች ያቃጥላል፤ ጦረኞች ድንፋታ፥ ጩኸትና የመለከት ድምፅ እያሰሙ የሞአብን ሕዝብ ይጨርሳሉ። የሞአብን ገዢና የአገሪቱንም ሹማምንት አጠፋለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕጌን ጥሰዋል፤ ትእዛዜንም አልጠበቁም፤ አባቶቻቸው ይከተሉአቸው የነበሩት የሐሰት አማልክት እነርሱንም አስተዋቸዋል፤ ስለዚህ በይሁዳ ምድር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ የኢየሩሳሌምንም ምሽጎች ያቃጥላል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ንጹሓንን በብር፥ ድኾችን በጫማ ይሸጡ ነበር። ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን በትቢያ ላይ ጥለው ራስ ራሳቸውን ይረግጣሉ፤ የተዋረዱ ምስኪኖችንም ገፍትረው ከመንገድ ያስወጣሉ፤ አባትና ልጅ ሁለቱም ከአንዲት ሴት ጋር ያመነዝራሉ፤ በዚህም ሥራቸው የተቀደሰውን ስሜን ያረክሳሉ። ዕዳቸውን መክፈል ከማይችሉ ድኾች ላይ ልብሳቸውን መያዣ አድርገው ይወስዳሉ፤ መሥዋዕት በሚያቀርቡበትም ቦታ ሁሉ ይተኙበታል፤ ከባለ ዕዳዎች በመቀጫ ስም የወሰዱትን የወይን ጠጅ በአምላካቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ይጠጣሉ። “እኔ ግን ለእናንተ ስል ቁመታቸው እንደ ሊባኖስ ዛፍ፥ ብርታታቸው እንደ ዋርካ ዛፍ የነበረውን አሞራውያንን ከነሥር መሠረታቸው ነቃቅዬ አጠፋሁላችሁ፤ ከግብጽ ምድር አውጥቼ አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ መራኋችሁ፤ የአሞራውያንንም ምድር ርስት አድርጌ ሰጠኋችሁ። ከወንዶች ልጆቻችሁ መካከል አንዳንዶቹን ነቢያት፥ ከወጣቶቻችሁም መካከል አንዳንዶቹን ናዝራውያን አድርጌ አስነሣሁላችሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ታዲያ ይህ እውነት አይደለምን? እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። እናንተ ግን ናዝራውያንን የወይን ጠጅ በማጠጣት አሳታችሁ፤ ነቢያትንም ትንቢት እንዳይናገሩ ከለከላችሁ። ስለዚህ ከመጠን በላይ እህል የተጫነ ሠረገላ በሥሩ ያለውን ነገር እንደሚጨፈልቅ እናንተንም እጨፈልቃችኋለሁ። ፈጣኑ ሯጭ መፍጠን ያቅተዋል፤ ብርቱ ሰዎችንም ኀይላቸው ይከዳቸዋል፤ ጦረኞችም ራሳቸውን ማዳን አይችሉም። ቀስት ወርዋሪዎች ቆመው አይመክቱም፤ ፈጣን ሯጮችም ሮጠው አያመልጡም፤ ፈረሰኞችም ሕይወታቸውን ማዳን አይችሉም። በዚያን ቀን እጅግ ብርቱ የሆኑ ጦረኞች እንኳ የጦር መሣሪያቸውን እየጣሉ ይሸሻሉ፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።