አሞጽ 2:1-16
አሞጽ 2:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የኤዶምያስን ንጉሥ አጥንት አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የሞዓብ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። በሞዓብ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የከተሞችዋንም መሠረቶች ትበላለች፤ ሞዓብም በድካምና በውካታ፥ በመለከትም ድምፅ ይሞታል፤ ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፤ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእግዚአብሔርን ሕግ አፍርሰዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉት ከንቱ ነገር አስቶአቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የይሁዳ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። በይሁዳ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የኢየሩሳሌምንም መሠረቶች ትበላለች።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ጻድቁን በብር፥ ችጋረኛውንም ምድርን በሚረግጡበት አንድ ጥንድ ጫማ ሸጠውታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የእስራኤል ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። የድሆችን ራስ ይቀጠቅጣሉ፤ የትሑታንንም ፍርድ ያጣምማሉ፤ የአምላካቸውንም ስም ያረክሱ ዘንድ አባትና ልጁ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤ ልብሳቸውንም አስረው ለመሥዊያው መጋረጃ ያደርጋሉ፤ በአምላካቸውም ቤት የቅሚያ ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ወይራ ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ። የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጐበዛዝቶቻችሁም ለእኔ የተለዩትን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ይህ እንደዚህ አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ ግን ለእኔ የተለዩትን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም፥ “ትንቢትን አትናገሩ ብላችሁ ከለከላችኋቸው። “ስለዚህ ሠረገላ ብርዑን እንዲያደቅ፥ በበታቻችሁ ባለ መሬት እኔ አደቅቃችኋለሁ። የሚሮጥ ሰው ማምለጥ አይችልም፤ ኀይለኛውም በብርታቱ አይዝም፤ አርበኛውም ነፍሱን አያድንም። ቀስተኛውም አይቆምም፤ ፈጣኑም አያመልጥም፤ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤ ልበ ሙሉው ኀይለኛም በኀይሉ አይተማመንም፤ ነገር ግን በዚያ ቀን ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል” ይላል እግዚአብሔር።
አሞጽ 2:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የሞዓብ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ የኤዶምን ንጉሥ ዐጥንት፣ ዐመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሏልና፤ የቂርዮትን ምሽጎች እንዲበላ፣ በሞዓብ ላይ እሳት እሰድዳለሁ፤ ሞዓብ በጦርነት ጩኸትና በመለከት ድምፅ መኻል፣ በታላቅ ሁካታ ውስጥ ይሞታል። ገዥዋን እደመስሳለሁ፣ አለቆቿንም ሁሉ ከንጉሧ ጋራ እገድላለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የይሁዳ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋል፤ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፤ አባቶቻቸው በተከተሏቸው አማልክት፣ በሐሰት አማልክት በመመራት ስተዋልና። የኢየሩሳሌምን ምሽጎች እንዲበላ፣ በይሁዳ ላይ እሳት እሰድዳለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የእስራኤል ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ጻድቁን ስለ ጥሬ ብር፣ ድኻውንም ስለ ጥንድ ጫማ ይሸጡታልና። የችግረኞችን ራስ፣ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ ፍትሕንም ከጭቍኖች ይነጥቃሉ፤ አባትና ልጅ ከአንዲት ሴት ጋራ ይተኛሉ፤ እንዲህም እያደረጉ ቅዱስ ስሜን ያረክሳሉ። በመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ፣ በየመሠዊያው ሥር ይተኛሉ፤ በአምላካቸው ቤት፣ በመቀጫነት የተወሰደውን የወይን ጠጅ ይጠጣሉ። “ቁመቱ እንደ ዝግባ፣ ጥንካሬውም እንደ ወርካ ዛፍ የነበረ ቢሆንም፣ አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁት፣ ከላይ ፍሬውን፣ ከታችም ሥሩን አጠፋሁ። የአሞራውያንን ምድር ልሰጣችሁ፣ ከግብጽ አወጣኋችሁ፤ አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መራኋችሁ። “ደግሞም ነቢያትን ከወንዶች ልጆቻችሁ መካከል፣ ናዝራውያንንም ከጕልማሶቻችሁ መካከል አስነሣሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ ይህ እውነት አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም ትንቢት እንዳይናገሩ አዘዛችኋቸው። “እነሆ፤ በእህል የተሞላ ጋሪ እንደሚያደቅቅ፣ እኔም አደቅቃችኋለሁ። ፈጣኑ አያመልጥም፤ ብርቱውንም ብርታቱ አይረዳውም፤ ኀያሉም ነፍሱን አያድንም። ቀስተኛው በቦታው ጸንቶ አይቆምም፤ ፈጣኑም ተዋጊ ሮጦ አያመልጥም፤ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም። ጐበዞቹ ተዋጊዎች እንኳ፣ በዚያ ቀን ዕራቍታቸውን ይሸሻሉ፤” ይላል እግዚአብሔር።
አሞጽ 2:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኤዶምያስን ንጉሥ አጥንት አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የሞዓብ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በሞዓብ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የቂርዮትንም አዳራሾች ትበላለች፥ ሞዓብም በውካታና በጩኸት በመለከትም ድምፅ ይሞታል፥ ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፥ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉት ሐሰታቸው አስቶአቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የይሁዳ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በይሁዳ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጻድቁን ስለ ብር፥ ችጋረኛውንም ስለ አንድ ጥንድ ጫማ ሽጠውታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የእስራኤል ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። የድሆችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፥ የትሑታንንም መንገድ ያጣምማሉ፥ ቅዱሱንም ስሜን ያረክሱ ዘንድ አባትና ልጁ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፥ በመሠዊያውም ሁሉ አጠገብ ለመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ ይተኛሉ፥ በአምላካቸውም ቤት ውስጥ በካሣ የተወሰደውን ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ኮምበል ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁ፥ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ። የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፥ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጐበዛዝቶቻችሁም ናዝራውያንን አስነሣሁ፥ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህ እንደዚህ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፥ ነቢያቱንም፦ ትንቢትን አትናገሩ ብላችሁ አዘዛችኋቸው። እነሆ፥ ነዶ የተሞላች ሰረገላ እንደምትደቀድቅ እንዲሁ እደቀድቃችኋለሁ። ከርዋጪም ሽሽት ይጠፋል፥ ብርቱውም በብርታቱ አይበረታም፥ ኃያሉም ነፍሱን አያድንም፥ ቀስተኛውም አይቆምም፥ ፈጣኑም አይድንም፥ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፥ በኃያላኑም መካከል ልበ ሙሉው በዚያ ቀን ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል፥ ይላል እግዚአብሔር።
አሞጽ 2:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሞአብ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የኤዶምን ንጉሥ ዐፅም ዐመድ እስኪሆን አቃጥለዋል፤ ስለዚህ በሞአብ ምድር እሳት እለቅበታለሁ፤ የቂሪዮትንም ምሽጎች ያቃጥላል፤ ጦረኞች ድንፋታ፥ ጩኸትና የመለከት ድምፅ እያሰሙ የሞአብን ሕዝብ ይጨርሳሉ። የሞአብን ገዢና የአገሪቱንም ሹማምንት አጠፋለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕጌን ጥሰዋል፤ ትእዛዜንም አልጠበቁም፤ አባቶቻቸው ይከተሉአቸው የነበሩት የሐሰት አማልክት እነርሱንም አስተዋቸዋል፤ ስለዚህ በይሁዳ ምድር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ የኢየሩሳሌምንም ምሽጎች ያቃጥላል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ንጹሓንን በብር፥ ድኾችን በጫማ ይሸጡ ነበር። ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን በትቢያ ላይ ጥለው ራስ ራሳቸውን ይረግጣሉ፤ የተዋረዱ ምስኪኖችንም ገፍትረው ከመንገድ ያስወጣሉ፤ አባትና ልጅ ሁለቱም ከአንዲት ሴት ጋር ያመነዝራሉ፤ በዚህም ሥራቸው የተቀደሰውን ስሜን ያረክሳሉ። ዕዳቸውን መክፈል ከማይችሉ ድኾች ላይ ልብሳቸውን መያዣ አድርገው ይወስዳሉ፤ መሥዋዕት በሚያቀርቡበትም ቦታ ሁሉ ይተኙበታል፤ ከባለ ዕዳዎች በመቀጫ ስም የወሰዱትን የወይን ጠጅ በአምላካቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ይጠጣሉ። “እኔ ግን ለእናንተ ስል ቁመታቸው እንደ ሊባኖስ ዛፍ፥ ብርታታቸው እንደ ዋርካ ዛፍ የነበረውን አሞራውያንን ከነሥር መሠረታቸው ነቃቅዬ አጠፋሁላችሁ፤ ከግብጽ ምድር አውጥቼ አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ መራኋችሁ፤ የአሞራውያንንም ምድር ርስት አድርጌ ሰጠኋችሁ። ከወንዶች ልጆቻችሁ መካከል አንዳንዶቹን ነቢያት፥ ከወጣቶቻችሁም መካከል አንዳንዶቹን ናዝራውያን አድርጌ አስነሣሁላችሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ታዲያ ይህ እውነት አይደለምን? እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። እናንተ ግን ናዝራውያንን የወይን ጠጅ በማጠጣት አሳታችሁ፤ ነቢያትንም ትንቢት እንዳይናገሩ ከለከላችሁ። ስለዚህ ከመጠን በላይ እህል የተጫነ ሠረገላ በሥሩ ያለውን ነገር እንደሚጨፈልቅ እናንተንም እጨፈልቃችኋለሁ። ፈጣኑ ሯጭ መፍጠን ያቅተዋል፤ ብርቱ ሰዎችንም ኀይላቸው ይከዳቸዋል፤ ጦረኞችም ራሳቸውን ማዳን አይችሉም። ቀስት ወርዋሪዎች ቆመው አይመክቱም፤ ፈጣን ሯጮችም ሮጠው አያመልጡም፤ ፈረሰኞችም ሕይወታቸውን ማዳን አይችሉም። በዚያን ቀን እጅግ ብርቱ የሆኑ ጦረኞች እንኳ የጦር መሣሪያቸውን እየጣሉ ይሸሻሉ፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።
አሞጽ 2:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የኤዶምያስን ንጉሥ ዐፅም አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎአልና ስለ ሦስት የሞዓብ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በሞዓብ ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የቂርዮትንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች፤ ሞዓብም በውካታና በጩኸት በመለከትም ድምፅ መካከል ይሞታል፤ ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፥ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ፥” ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “የጌታን ሕግ ጥለዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉአቸው ሐሰቶቻቸው አስተዋቸዋልና ስለ ሦስት የይሁዳ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በይሁዳ ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ ጻድቁን ስለ ብር፥ ችግረኛውንም ስለ አንድ ጥንድ ጫማ ሸጠዋልና ስለ ሦስት የእስራኤል ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። የድሆችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ የትሑታንንም መንገድ ያጣምማሉ፤ ቅዱሱንም ስሜን ለማርከስ አባትና ልጅ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤ በመሠዊያውም ሁሉ አጠገብ ለመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ ይተኛሉ፤ በአምላካቸውም ቤት ውስጥ በካሣ የተወሰደውን ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። “እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ባሉጥ ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው ደመሰስሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ። እኔም ከግብጽም ምድር አወጣኋችሁ፥ የአሞራዊውንም ምድር እንድትወርሱ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጉልማሶቻችሁም ናዝራውያንን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ይህ በእውነት እንደዚህ አይደለምን?” ይላል ጌታ። እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችሁ፤ ነቢያቱንም፦ ትንቢትን አትናገሩ፥ ብላችሁ አዘዛችሁ። “እነሆ፥ እህል የተሞላ ሠረገላ እንደሚያደቅቅ፥ እንዲሁም እኔ በመሬታችሁ ላይ አደቅቃችኋለሁ። ፈጣኑ ሯጭ መሸሽ ሳይችል ይጠፋል፥ ብርቱውም በብርታቱ አይበረታም፥ ኃያሉም ነፍሱን አያድንም፤ ቀስተኛውም አይቆምም፥ ፈጣኑም ሯጭ አያመልጥም፥ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤ በዚያ ቀን በኃያላኑም መካከል ልበ ሙሉው ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል፥” ይላል ጌታ።