አምጥተውም በሸንጎው ፊት አቆሙአቸው፤ የካህናት አለቃውም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “የኢየሱስን ስም በመጥራት እንዳታስተምሩ በጥብቅ አዘናችሁ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ እናንተ ለዚያ ሰው ሞት እኛን ተጠያቂዎች ልታደርጉን ትፈልጋላችሁ።” ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት ግን እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ለሰው ከመታዘዝ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባናል፤ የአባቶቻችን አምላክ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን ከሞት አስነሣው፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ንስሓንና የኃጢአትን ይቅርታ እንዲሰጥ ኢየሱስን መሪና አዳኝ አድርጎ በቀኙ በክብር እንዲቀመጥ አድርጎታል፤ ስለዚህ ነገር እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ የሰጣቸው መንፈስ ቅዱስም ምስክር ነው።” የሸንጎ አባሎች ይህን በሰሙ ጊዜ በጣም ተቈጥተው ሐዋርያቱን ለመግደል ፈለጉ። ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ የተከበረና የሕግ መምህር የሆነ፥ ገማልያል የተባለ አንድ ፈሪሳዊ የሸንጎ አባል ተነሣና ለጥቂት ጊዜ ሐዋርያቱን ገለል እንዲያደርጉአቸው አዘዘ። ከዚህ በኋላ የሸንጎውን አባሎች እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በእነዚህ ሰዎች ላይ በምታደርጉት ነገር ተጠንቀቁ። ከዚህ በፊት ቴዎዳስ የሚባል ሰው ‘እኔ ትልቅ ሰው ነኝ’ ብሎ ተነሥቶ ነበር፤ አራት መቶ የሚያኽሉም ሰዎች ከእርሱ ጋር ተባብረው ነበር። ነገር ግን እርሱ ተገደለ፤ ተከታዮቹ ተበታተኑ፤ ዓላማውም እንዳልነበረ ሆነ። ከዚያም በኋላ የሕዝብ ቈጠራ በተደረገበት ዘመን ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሰዎች እንዲከተሉት አድርጎ ነበር፤ እርሱም ተገደለ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። ስለዚህ አሁንም እኔ የምላችሁ ከነዚህ ሰዎች እንድትርቁና እንድትተዉአቸው ነው፤ ይህ አሳብ ወይም ሥራ ከሰው የመጣ ከሆነ ይጠፋል። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን እነርሱን ልታጠፉአቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ይሆንባችኋል።” እነርሱም የገማልያልን ምክር ተቀበሉ። ከዚህ በኋላ ሐዋርያቱን ወደ እነርሱ ጠርተው አስገረፉአቸው፤ የኢየሱስንም ስም በመጥራት እንዳይናገሩ አዘዙአቸውና ለቀቁአቸው። ሐዋርያት ግን ስለ ኢየሱስ ስም ውርደት ለመቀበል የተገቡ በመሆናቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ በየቀኑም በቤተ መቅደስና በየቤቱም ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ ማስተማርንና የምሥራች መናገርን አላቋረጡም ነበር።
የሐዋርያት ሥራ 5 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 5:27-42
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos