ሐዋርያትንም አምጥተው በሸንጎው ፊት አቆሟቸው፤ ሊቀ ካህናቱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ ደግሞም እኛን ለዚህ ሰው ደም ተጠያቂዎች ልታደርጉን ቈርጣችሁ ተነሣችሁ።” ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉ፤ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል! እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፣ የአባቶቻችን አምላክ ከሙታን አስነሣው፤ እርሱም ለእስራኤል ንስሓንና የኀጢአትን ስርየት ይሰጥ ዘንድ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኝ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። እኛም ለእነዚህ ነገሮች ምስክር ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ። ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤ ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል። ከዚህ ቀደም፣ ቴዎዳስ ራሱን ትልቅ አድርጎ በመቍጠር ተነሥቶ፣ አራት መቶ ያህል ሰዎች ተባበሩት፤ ነገር ግን እርሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ፤ ነገሩም እንዳልነበር ሆነ። ከርሱም በኋላ፣ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ አሸፈተ፤ ተከታይም አግኝቶ ነበር፤ እርሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ተበተኑ። ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው! አትንኳቸው! ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋራ ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።” እነርሱም ምክሩን ተቀብለው ሐዋርያትን አስጠርተው አስገረፏቸው፤ ዳግመኛም በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ለቀቋቸው። ሐዋርያትም፣ ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 5
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 5:27-42
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos