የሐዋርያት ሥራ 4:1-12

የሐዋርያት ሥራ 4:1-12 አማ05

ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ ሲናገሩ ሳሉ ካህናትና የቤተ መቅደሱ የዘበኞች አለቃ እንዲሁም ሰዱቃውያን ወደ እነርሱ መጡና ሁለቱ ሐዋርያት የኢየሱስን ከሞት መነሣት ለሕዝቡ በማስተማራቸውና በዚህም የሙታን ትንሣኤ መኖሩን በማስረዳታቸው ተቈጡ። ስለዚህ ያዙአቸውና ጊዜው መሽቶ ስለ ነበረ እስከ ማግስቱ ድረስ በወህኒ ቤት እንዲቈዩ አደረጉአቸው። ነገር ግን ቃላቸውን ከሰሙት ሰዎች ብዙዎቹ አመኑ፤ የአመኑትም ሰዎች ቊጥር ወደ አምስት ሺህ ከፍ አለ። በማግስቱ የአይሁድ አለቆችና ሽማግሌዎች፥ የሕግ መምህራንም በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል የካህናት አለቃው ሐናና ቀያፋ፥ ዮሐንስና እስክንድሮስ፥ የካህናት አለቃው ቤተሰቦች ሁሉ ይገኙባቸዋል፤ እነርሱም ሁለቱን ሐዋርያት በመካከላቸው አቁመው፥ “ይህን ያደረጋችኹት በምን ኀይል ወይም በማን ስም ነው?” ሲሉ ጠየቁአቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች ሆይ! እኛ ዛሬ የምንጠየቀው ለአንድ ሽባ ሰው ስለ ተደረገለት መልካም ሥራና በምን ዐይነት ሁኔታ እንደ ዳነ ነው። ይህ ሰው ድኖ በፊታችሁ የቆመው እናንተ በሰቀላችሁትና እግዚአብሔር ግን ከሞት ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንደ ሆነ ለእናንተ ለሁላችሁና ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች ንቃችሁ የጣላችሁትም ድንጋይ እርሱ ነው፤ ነገር ግን እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ። ስለዚህ መዳን ከእርሱ በቀር በሌላ በማንም የለም፤ እኛ ልንድንበት የሚገባን እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው ስም ከእርሱ በቀር በመላው ዓለም ማንም የለም።”