ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ እየተናገሩ ሳሉ፣ ካህናትና የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ኀላፊ እንዲሁም ሰዱቃውያን ድንገት ወደ እነርሱ መጡ። እነርሱም ሐዋርያት ሕዝቡን በማስተማራቸውና በኢየሱስ ስለ ተገኘው ትንሣኤ ሙታን በመስበካቸው እጅግ ተቈጡ። ጴጥሮስና ዮሐንስን ያዟቸው፤ ጊዜውም ምሽት ስለ ነበረ እስኪነጋ ድረስ ወህኒ ቤት አሳደሯቸው። ይሁን እንጂ ቃሉን ከሰሙት መካከል ብዙዎቹ አመኑ፤ የወንዶቹም ቍጥር ወደ ዐምስት ሺሕ ከፍ አለ። በማግስቱም አለቆቻቸውና፣ ሽማግሌዎቻቸው እንዲሁም ጸሐፍት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሊቀ ካህናቱ ሐና፣ ቀያፋ፣ ዮሐንስ፣ እስክንድሮስና የሊቀ ካህናቱ ቤተ ዘመዶች ሁሉ በዚያ ተገኝተው ነበር። እነርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን በመካከል አቁመው፣ “ይህን ያደረጋችሁት በምን ኀይል ወይም በማን ስም ነው?” ብለው ጠየቋቸው። በዚህ ጊዜ፣ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች ሆይ፤ ዛሬ ለዚህ ሽባ ሰው ስለ ተደረገው በጎ ሥራ፣ እንዴት እንደ ዳነ የምትጠይቁን ከሆነ፣ እናንተ በሰቀላችሁት፣ እግዚአብሔር ግን ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መዳኑንና ፊታችሁ መቆሙን እናንተም ሆናችሁ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይህን ይወቅ። እርሱም፣ “ ‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማእዘን ራስ የሆነው ድንጋይ’ ነው። ድነት በሌላ በማንም አይገኝም፤ እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠ ከዚህ ስም በቀር ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለምና።”
ሐዋርያት ሥራ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 4:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች