የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 28:1-15

የሐዋርያት ሥራ 28:1-15 አማ05

ወደ ምድር በደኅና ከደረስን በኋላ የደረስንባት ደሴት ማልታ የምትባል መሆንዋን ዐወቅን። የዚያች ደሴት ነዋሪዎች የሚያስደንቅ ደግነት አደረጉልን፤ በዚያን ጊዜም ዝናብ ስለ ዘነበና ብርድ ስለ ሆነ እሳት አንድደው ተቀበሉን፤ ጳውሎስ ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጥል፥ ከሙቀቱ የተነሣ አንድ እባብ ወጣና በእጁ ላይ ተጣብቆ ተንጠለጠለ፤ የማልታ ሰዎች እባብ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥሎ ባዩ ጊዜ “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው! ከባሕሩ ማዕበል በደኅና ቢወጣም ከአምላክ ፍርድ አምልጦ በሕይወት ለመኖር አልቻለም” ተባባሉ። ጳውሎስ ግን እባቡን ወደ እሳቱ አራግፎ ጣለውና ምንም ጒዳት ሳያገኘው ቀረ። ሰዎቹም “ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል፤ ወይም በድንገት ሞቶ ይወድቃል” በማለት ይጠባበቁ ነበር። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተጠባብቀውት ምንም ጒዳት እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ አሳባቸውን ለወጡና “ይህስ አምላክ ነው!” አሉ። በዚያ በነበርንበት ስፍራ አጠገብ የደሴቲቱ ገዢ የፑፕልዮስ መሬት ነበር፤ ይህ ሰው በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በጥሩ ሁኔታ አስተናገደን። በዚያን ጊዜ የፑፕልዮስ አባት ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስ ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም ጫነበትና ፈወሰው። ይህ ከሆነ በኋላ በደሴቲቱ የሚኖሩት ሌሎች በሽተኞች መጡና ተፈወሱ። ሰዎቹ ብዙ ስጦታ አመጡልን፤ አክብሮታቸውንም ገለጡልን፤ በመርከብ ለመሄድ በተነሣንም ጊዜ የሚያስፈልገንን ሁሉ በመርከብ ላይ ጫኑልን። ሦስት ወር በማልታ ከቈየን በኋላ ክረምቱን በደሴቲቱ ባሳለፈው በእስክንድርያው መርከብ ተሳፍረን ተነሣን፤ መርከቡ ዲዮስቆሮስ የተባሉ የመንታ አማልክት አርማ ነበረበት። ወደ ስራኩስ ከተማ በደረስን ጊዜ እዚያ ሦስት ቀን ተቀመጥን። ከዚያም በባሕሩ ዞረን ወደ ሬጊዩም ከተማ ደረስን፤ እዚያ አንድ ቀን ካሳለፍን በኋላ የደቡብ ነፋስ ስለ ነፈሰ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ሄድን። እዚያ ወንድሞችን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሮም ሄድን። በሮም ያሉ ምእመናን ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ እስከ አፍዮስ ገበያና “ሦስት ማደሪያዎች” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን መጡ፤ ጳውሎስ እነርሱን ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነና ተጽናና።