በደኅና ወደ ምድር ከደረስን በኋላ፣ ደሴቲቱ መላጥያ ተብላ እንደምትጠራ ተረዳን። የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስም ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጨምር፣ ከሙቀቱ የተነሣ እፉኝት ወጥታ እጁ ላይ ተጣበቀች። የደሴቲቱ ነዋሪዎች እባብ በእጁ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ነፍስ ገዳይ ነው፤ ከባሕር ቢያመልጥ እንኳ የፍርድ አምላክ በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ተባባሉ። ጳውሎስ ግን እባቢቱን ወደ እሳቱ አራገፋት፤ አንዳችም ጕዳት አልደረሰበትም። ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ሞቶ ይወድቃል ብለው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጠብቀው ምንም የተለየ ነገር እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ፣ ሐሳባቸውን ለውጠው፣ “ይህስ አምላክ ነው” አሉ። በዚያም ስፍራ አጠገብ የደሴቲቱ አለቃ የፑፕልዮስ ርስት የሆነ መሬት ነበረ፤ እርሱም በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በቸርነት አስተናገደን። የፑፕልዮስም አባት በትኵሳትና በተቅማጥ ሕመም ተይዞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ሊጠይቀው ገብቶ ከጸለየለት በኋላ፣ እጁን ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ፣ በደሴቲቱ የነበሩ ሌሎች ሕመምተኞችም እየመጡ ተፈወሱ። እኛንም በብዙ መንገድ አከበሩን፤ በመርከብም ለመሄድ በተዘጋጀን ጊዜ፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ ጫኑልን። ከሦስት ወር በኋላም፣ በደሴቲቱ ክረምቱን ቆሞ በሰነበተ በአንድ መርከብ ተነሥተን ጕዞ ጀመርን። ይህም መርከብ የእስክንድርያ ሲሆን፣ በላዩ ላይ የመንታ አማልክቱ የዲዮስቆሮስ አርማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስ ከተማ ገብተን ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጥን። ከዚያም በመርከብ ተጕዘን ሬጊዩም ደረስን፤ በማግስቱም የደቡብ ነፋስ ስለ ተነሣ ፑቲዮሉስ የደረስነው በሚቀጥለው ቀን ነበር። በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነርሱም ሰባት ቀን አብረናቸው እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሮም ሄድን። በዚያ የነበሩ ወንድሞችም መምጣታችንን ስለ ሰሙ፣ እስከ አፍዩስ ፋሩስ እንዲሁም “ሦስት ማደሪያ” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም።
ሐዋርያት ሥራ 28 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 28
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 28:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos