ወደ ኢጣሊያ በመርከብ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ ጳውሎስንና ሌሎችንም እስረኞች በአውግስጦስ ክፍለ ጦር ውስጥ ለነበረው ዩልዮስ ለሚባለው መቶ አለቃ አስረከቡአቸው። በእስያ የባሕር ዳርቻ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው የአድራሚጥዮን መርከብ ተሳፍረን ተጓዝን፤ በተሰሎንቄ የሚኖረው የመቄዶንያው ሰው አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋር ነበረ። በማግስቱ ወደ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስ ለጳውሎስ ደግ ስለ ነበረ ወደ ወዳጆቹ ሄዶ የሚያስፈልገውን ርዳታ እንዲያደርጉለት ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ከፊት ለፊት ይነፍስብን ስለ ነበር የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን በመርከብ ጒዞአችንን ቀጠልን። በኪልቅያና በጵንፍልያ አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሊቅያ አገር ወዳለው ወደ ሙራ ከተማ ደረስን። እዚያ የመቶ አለቃው ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ አገኘና በእርሱ ላይ እንድንሳፈር አደረገ። ብዙ ቀን ቀስ እያልን ተጒዘን በብዙ ችግር ወደ ቀኒዶስ ከተማ አጠገብ ደረስን፤ ነፋሱም ወደፊት እንዳንሄድ ስለ ከለከለን በሰልሞና ርእሰ ምድር ጫፍ አጠገብ አለፍንና የቀርጤስን ደሴት ተገን አድርገን ሄድን። በብዙ ችግር ጥግ ጥጉን ካለፍን በኋላ በላስያ ከተማ አጠገብ ወደምትገኘው “መልካም ወደብ” ወደምትባለው ስፍራ ደረስን። በጒዞአችን ላይ ብዙ ጊዜ በመባከኑና የጾም ጊዜ በማለፉ ምክንያት በዚህ ጊዜ በባሕር ላይ መጓዝ አደገኛ ስለ ነበር ጳውሎስ ለሰዎቹ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው፤ “እናንተ ሰዎች! ከእንግዲህ ወዲህ ያለው ጒዞአችን አደጋ እንዳለበት ይታየኛል፤ በጭነቱና በመርከቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ሕይወትም ላይ ብርቱ ጒዳትና ጥፋት ይደርሳል።” የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ አዛዥና የመርከቡ ባለቤት የሚሉትን ይሰማ ነበር። ያ ወደብ ለክረምት ማሳለፊያ ምቹ ስላልነበረ አብዛኞቹ ሰዎች “ጒዞአቸውን ቀጥለው የሚቻል ቢሆን በሰሜን ምዕራብና በደቡብ ምዕራብ በር ወዳለው ፊንቄ ወደሚባለው የቀርጤስ ወደብ ደርሰን ክረምቱን እዚያ እናሳልፍ” ብለው አሳብ አቀረቡ። አነስተኛ የደቡብ ነፋስ ሲነፍስ ባዩ ጊዜ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው መልሕቃቸውን አንሥተው ጒዞአቸውን ለመቀጠል ተነሡ፤ ከወደቡም ተነሥተው በቀርጤስ አጠገብ አድርገው ጥግ ጥጉን አለፉ። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ “የሰሜናዊ ምሥራቅ ዐውሎ ነፋስ” የሚባል ኀይለኛ ነፋስ ከደሴቲቱ ተነሥቶ ወደ ባሕሩ መጣባቸው። መርከቡም ስለ ተገፋና ነፋሱን መቋቋም ስላልቻለ ዝም ብለን በነፋሱ እየተነዳን ሄድን። ቄዳ የተባለችውን ደሴት ተገን አድርገን ስንጓዝ በታላቅ ችግር የመርከቡን ጀልባ ይዘን በቊጥጥራችን ሥር ለማድረግ ቻልን። መርከበኞቹ ጀልባውን ወደ መርከቡ ስበው ካወጡት በኋላ በመርከቡ ዙሪያ ገመድ ጠመጠሙ፤ መርከቡ ሱርቲስ ወደምትባል አሸዋማ ስፍራ እንዳይወድቅ ፈርተው ሸራውን አወረዱና በነፋስ እየተነዱ ሄዱ። ዐውሎ ነፋሱ እየበረታብን ስለ ሄደ በማግስቱ በመርከቡ ላይ ከተጫኑት ዕቃዎች እያንዳንዱን ወደ ባሕር መጣል ጀመሩ። በሦስተኛውም ቀን ለመርከቡ የሚያገለግሉትን ዕቃዎች በገዛ እጃቸው እየወረወሩ ጣሉ፤ ለብዙ ቀን ፀሐይም ሆነ፤ ከዋክብት ስላልታዩና ነፋሱም እየበረታብን ስለ ሄደ ከእንግዲህ ወዲህ መዳን አንችልም ብለን ተስፋ ቈረጥን። ሰዎቹ ምንም ምግብ ሳይበሉ ብዙ ቀን ቈዩ፤ ስለዚህ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች! እኔ ያልኳችሁን ሰምታችሁ ከቀርጤስ ባትነሡ ኖሮ ይህ ሁሉ ጒዳትና ጥፋት ባልደረሰባችሁም ነበር። አሁንም መርከቡ ብቻ ይጐዳል እንጂ ከእናንተ በማንም ላይ ጥፋት አይደርስም፤ ስለዚህ አይዞአችሁ፤ አትፍሩ! ብዬ እመክራችኋለሁ። ባለፈው ሌሊት የእርሱ የሆንኩ የማመልከው አምላክ የላከው መልአክ በአጠገቤ ቆሞ ‘ጳውሎስ ሆይ! አትፍራ! በሮም ንጉሠ ነገሥት ፊት መቆም ይገባሃል! እነሆ፥ ከአንተ ጋር የሚጓዙትንም ሁሉ እግዚአብሔር ለአንተ ብሎ ከሞት ያድናቸዋል’ ብሎ ነግሮኛል። ስለዚህ እናንተ ሰዎች አይዞአችሁ! እግዚአብሔር ይህንን የነገረኝን ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽም አምነዋለሁ።
የሐዋርያት ሥራ 27 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 27:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች