የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 22:22-30

የሐዋርያት ሥራ 22:22-30 አማ05

እስከዚህ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ የጳውሎስን ንግግር ያዳምጡ ነበር፤ ከዚህ በኋላ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፦ “እንዲህ ዐይነቱ ሰው ከምድር ላይ ይወገድ! እንዲህ ዐይነቱ ሰው በሕይወት መኖር አይገባውም!” እያሉ ጮኹ። እነርሱ እየጮኹ ልብሳቸውን ያውለበልቡና ዐፈር ወደ ሰማይ ይበትኑ ነበር። አዛዡ ይህን ባየ ጊዜ ጳውሎስን ወደ ወታደሮች ሰፈር እንዲያስገቡት አዘዘ፤ ሕዝቡ በእርሱ ላይ ስለምን ይህን ያኽል እንደሚጮኹ ለማወቅም እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ። ነገር ግን በጠፍር ወጥረው ሊገርፉት ሲዘጋጁ ጳውሎስ አጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ “የሮም ዜግነት ያለውን ሰው ያለ ፍርድ ልትገርፉት ተፈቅዶላችኋልን?” አለው። የመቶ አለቃው ይህን በሰማ ጊዜ ወደ አዛዡ ሄደና “ምን ልታደርግ ነው? ይህ ሰው እኮ የሮም ዜጋ ነው!” አለው። ስለዚህ አዛዡ ወደ ጳውሎስ ቀረብ አለና “እስቲ ንገረኝ፤ አንተ የሮም ዜጋ ነህን?” አለው፤ እርሱም “አዎ፥ ነኝ፤” አለ። አዛዡም “እኔ ይህን ዜግነት የገዛሁት በብዙ ገንዘብ ነው” አለ፤ ጳውሎስም “እኔ ግን በሮም ዜግነት ተወልጄአለሁ” አለ። ስለዚህ እነዚያ ሊመረምሩት ተዘጋጅተው የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ከእርሱ ራቁ፤ አዛዡም የሮም ዜጋ የሆነውን ሰው በሰንሰለት ማሰሩን በተገነዘበ ጊዜ ፈራ። በማግስቱ አዛዡ፥ አይሁድ ጳውሎስን የከሰሱበት ትክክለኛ ምክንያት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ፈለገ፤ ስለዚህ የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም ከእስራቱ ፈቶ ወሰደና በፊታቸው አቀረበው።