የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 22:22-30

ሐዋርያት ሥራ 22:22-30 NASV

ሕዝቡም ይህን ቃል እስኪናገር ድረስ ሰሙት፤ ከዚህ በኋላ ግን ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ፣ “ይህስ ከምድር ገጽ ይወገድ! በሕይወት መኖር አይገባውም!” ብለው ጮኹበት። እነርሱም እየጮኹና ልብሳቸውን እየወረወሩ፣ ትቢያም ወደ ላይ እየበተኑ ሳሉ፣ የጦር አዛዡ ጳውሎስን ወደ ጦር ሰፈር እንዲያስገቡትና ሕዝቡ ለምን እንዲህ እንደሚጮኹበት እየተገረፈ እንዲመረመር ትእዛዝ ሰጠ። ጳውሎስም በጠፍር ወጥረው ሊገርፉት ሲሉ፣ አጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ፣ “አንድን የሮም ዜጋ ያለ ፍርድ ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋልን?” አለው። የመቶ አለቃውም ይህን ሲሰማ፣ ወደ ጦር አዛዡ ቀርቦ፣ “ምን እያደረግህ እንደ ሆነ ዐውቀሃል? ሰውየው እኮ ሮማዊ ነው” አለው። አዛዡም ወደ ጳውሎስ ቀርቦ፣ “አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ፤ ሮማዊ ነህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፤ ነኝ” አለው። አዛዡም መልሶ፣ “እኔ ይህን ዜግነት ያገኘሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” አለ። ጳውሎስም፣ “እኔ ግን ከተወለድሁ ጀምሮ ሮማዊ ነኝ” አለው። ስለዚህ እነዚያ ሊመረምሩት ያሰቡት ሰዎች ወዲያው ከርሱ ሸሹ፤ የጦር አዛዡም የሮም ዜጋ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ በሰንሰለት አስሮት ስለ ነበር ፈራ። በማግስቱም የጦር አዛዡ፣ አይሁድ ጳውሎስን የከሰሱበት ትክክለኛው ምክንያት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ስለ ፈለገ ፈታው፤ ከዚያም የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባላት በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።