የሐዋርያት ሥራ 21:1-14

የሐዋርያት ሥራ 21:1-14 አማ05

ከእነርሱ ከተለየን በኋላ በመርከብ ተሳፈርንና በቀጥታ ቆስ ወደምትባል ደሴት ሄድን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ ደሴት ደረስን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ከተማ ሄድን። እዚያም ወደ ፊንቄ አገር የምትሄድ መርከብ አገኘንና በእርስዋ ተሳፍረን፤ ጒዞአችንን ቀጠልን። የቆጵሮስን ደሴት በስተግራችን ትተን ወደ ሶርያ አገር ተጓዝንና ወደ ጢሮስ ወደብ ሄድን፤ መርከቡ ጭነቱን እዚያ ማራገፍ ነበረበት። እዚያ ምእመናንን ፈልገን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን ቈየን። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ” ብለው ነገሩት። እዚያ የምንቈይበት ጊዜ ሲያልቅ ተለይተናቸው ጒዞአችንን ቀጠልን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው እስከ ከተማው ውጪ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ከጸለይን በኋላ ተሰነባበትን። ከዚህ በኋላ እኛ በመርከብ ስንሳፈር እነርሱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከጢሮስ ተነሥተን ወደ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያ ከአማኞች ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ከእነርሱ ጋር አንድ ቀን አሳለፍን። በማግስቱ ከዚያ ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ እዚያ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገባንና ከእርሱ ጋር ተቀመጥን። እርሱ ትንቢት የመናገር ስጦታ ያላቸው አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ነበሩት። ለብዙ ቀኖች እዚያ በተቀመጥንበት ጊዜ አጋቦስ የሚባል ነቢይ ከይሁዳ ምድር መጣ። ይህ ነቢይ ወደ እኛ ቀረበ፤ የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጆቹንና እግሮቹን አሰረና “መንፈስ ቅዱስ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ እንደዚህ አስረው ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል” አለ። ይህንን በሰማን ጊዜ እኛም እዚያ የነበሩ ሰዎችም ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። ጳውሎስ ግን “እንደዚህ እያለቀሳችሁ ስለምን ልቤን በሐዘን ትሰብሩታላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ። ምክራችንን አልቀበልም ባለን ጊዜ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው።