ሐዋርያት ሥራ 21:1-14
ሐዋርያት ሥራ 21:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከእነርሱም ከተለየን በኋላ እኛ በመርከብ ተሳፍረን፥ መንገዳችንንም አቅንተን ወደ ቆስ መጣን፤ በበነጋውም ወደ ሮዶስ፥ ከዚያም ወደ ጳጥራ ገባን። ወደ ፊንቄም የሚያልፍ መርከብ አግኝተን በዚያ ላይ ተሳፍረን ሄድን። ቆጵሮስንም አየናት፤ በስተ ግራችንም ትተናት ወደ ሶርያ ሄድን፤ ወደ ጢሮስም ወረድን፤ በመርከብ ያለውን ጭነት ሁሉ በዚያ ያራግፉ ነበርና። በዚያም ደቀ መዛሙርትን አገኘንና በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ነገሩት። ከዚህም በኋላ ለመሄድ ወጣን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን። እርስ በርሳችንም ተሳስመን ተሰነባበትን፤ ከዚህም በኋላ ወደ መርከብ ወጣን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም ከጢሮስ ወጥተን አካ ወደምትባል ሀገር መጣን፤ ወንድሞቻችንንም አግኝተን ሰላም አልናቸው፤ በእነርሱም ዘንድ አንድ ቀን አደርን። በማግሥቱም ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ ወደ ወንጌላዊው ወደ ፊልጶስ ቤትም ገባን፤ እርሱም ከሰባቱ ወንድሞች ዲያቆናት አንዱ ነው። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። በእርሱም ዘንድ ብዙ ቀን ኖርን፤ ከይሁዳም አጋቦስ የሚባል አንድ ነቢይ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ እጁንና እግሩን በገዛ እጁ አስሮ እንዲህ አለ፥ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ የዚህን መታጠቂያ ጌታ አይሁድ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።” ይህንም ሰምተን የሀገሪቱን ሰዎች ይዘን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ጳውሎስን ማለድነው። ጳውሎስ ግን መልሶ፥ “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? እያለቀሳችሁ ልቤን ትሰብሩታላችሁ፤ እኔ እኮ ተስፋ የማደርገው መከራንና እግር ብረትን ብቻ አይደለም፤ እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞትም ቢሆን የቈረጥሁ ነኝ” አለ። እንቢ ባለ ጊዜም ዝም አልን፤ እኛም እግዚአብሔር የፈቀደው ይሁን ብለን ተውነው።
ሐዋርያት ሥራ 21:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእነርሱ ከተለየን በኋላ ቀጥታ በመርከብ ወደ ቆስ ተጓዝን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ፣ ከዚያም ወደ ጳጥራ አመራን። በዚያም ወደ ፊንቄ የሚሄድ መርከብ ስላገኘን፣ ተሳፍረን ጕዟችንን ቀጠልን። ቆጵሮስ በታየችን ጊዜ፣ ወደ ግራ ትተናት ዐለፍንና ወደ ሶርያ አመራን፤ መርከባችን ጭነቱን በጢሮስ ማራገፍ ስለ ነበረበት እኛም እዚያው ወረድን። ደቀ መዛሙርትንም በዚያ አግኝተን፣ ሰባት ቀን ከእነርሱ ጋራ ተቀመጥን። እነርሱም በመንፈስ ሆነው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ነገሩት። የቈይታ ጊዜያችን ባለቀ ጊዜ፣ ትተናቸው ጕዟችንን ቀጠልን፤ ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ ከተሰነባበትንም በኋላ እኛ ወደ መርከቡ ገባን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከጢሮስ ተነሥተን ጕዟችንን በመቀጠል ጴጤሌማይስ ደረስን፤ ከመርከብ ወርደንም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ፣ አንድ ቀን ከእነርሱ ጋራ ቈየን። በማግስቱም ከዚያ ተነሥተን ቂሳርያ ደረስን፤ ከሰባቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው በፊልጶስ ቤትም ዐረፍን። እርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ የተባለ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ፤ ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወሰደ፤ የራሱንም እጅና እግር በማሰር፣ “መንፈስ ቅዱስ፣ ‘በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት እንዲህ አድርገው በማሰር ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል’ ይላል” አለ። ይህን ስንሰማ እኛና በዚያም የሚኖሩት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። ጳውሎስ ግን፣ “ለምን እንዲህ እያለቀሳችሁ ልቤን ታባቡታላችሁ? እኔ መታሰር ቀርቶ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ዝግጁ ነኝ” አላቸው። ምክራችንን አልቀበል ስላለን፣ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው።
ሐዋርያት ሥራ 21:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፥ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት። ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፥ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንም ተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፥ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፥ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ፦ እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ፦ ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ፦ እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ። ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ፦ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን።
ሐዋርያት ሥራ 21:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእነርሱ ከተለየን በኋላ በመርከብ ተሳፈርንና በቀጥታ ቆስ ወደምትባል ደሴት ሄድን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ ደሴት ደረስን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ከተማ ሄድን። እዚያም ወደ ፊንቄ አገር የምትሄድ መርከብ አገኘንና በእርስዋ ተሳፍረን፤ ጒዞአችንን ቀጠልን። የቆጵሮስን ደሴት በስተግራችን ትተን ወደ ሶርያ አገር ተጓዝንና ወደ ጢሮስ ወደብ ሄድን፤ መርከቡ ጭነቱን እዚያ ማራገፍ ነበረበት። እዚያ ምእመናንን ፈልገን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን ቈየን። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ” ብለው ነገሩት። እዚያ የምንቈይበት ጊዜ ሲያልቅ ተለይተናቸው ጒዞአችንን ቀጠልን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው እስከ ከተማው ውጪ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ከጸለይን በኋላ ተሰነባበትን። ከዚህ በኋላ እኛ በመርከብ ስንሳፈር እነርሱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከጢሮስ ተነሥተን ወደ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያ ከአማኞች ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ከእነርሱ ጋር አንድ ቀን አሳለፍን። በማግስቱ ከዚያ ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ እዚያ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገባንና ከእርሱ ጋር ተቀመጥን። እርሱ ትንቢት የመናገር ስጦታ ያላቸው አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ነበሩት። ለብዙ ቀኖች እዚያ በተቀመጥንበት ጊዜ አጋቦስ የሚባል ነቢይ ከይሁዳ ምድር መጣ። ይህ ነቢይ ወደ እኛ ቀረበ፤ የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጆቹንና እግሮቹን አሰረና “መንፈስ ቅዱስ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ እንደዚህ አስረው ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል” አለ። ይህንን በሰማን ጊዜ እኛም እዚያ የነበሩ ሰዎችም ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። ጳውሎስ ግን “እንደዚህ እያለቀሳችሁ ስለምን ልቤን በሐዘን ትሰብሩታላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ። ምክራችንን አልቀበልም ባለን ጊዜ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው።
ሐዋርያት ሥራ 21:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት፤ ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፤ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ ተመርተው ነገሩት። ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንምተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፤ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፤ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፤ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ “እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ‘ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል፤ በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል፤’ ይላል፤” አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ “እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም፤” አለ። ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ “የጌታ ፈቃድ ይሁን፤” ብለን ዝም አልን።