የሐዋርያት ሥራ 19:1-10

የሐዋርያት ሥራ 19:1-10 አማ05

አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን ደረሰ፤ እዚያ ጥቂት ክርስቲያኖችን አገኘና “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችሁ ነበርን?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አልተቀበልንም፤ መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ ሰምተን አናውቅም” ሲሉ መለሱለት። ጳውሎስም “ታዲያ፥ ምን ዐይነት ጥምቀት ነው የተጠመቃችሁት?” አላቸው። እነርሱም “የዮሐንስን ጥምቀት ነው” አሉት። ጳውሎስም “የዮሐንስ ጥምቀትማ ንስሓ ስለ መግባት የተፈጸመ ነው፤ ለሕዝቡም የተናገረው ‘ከእኔ በኋላ በሚመጣው እመኑ’ እያለ ነበር፤ እርሱም ኢየሱስ ነው” አላቸው። ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። ጳውሎስ እጁን በጫነባቸውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረደና በሌላ ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትንም መናገር ጀመሩ። ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያኽል ነበሩ። ጳውሎስ ወደ ምኲራብ ሄዶ ለሦስት ወር ያኽል ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተከራከረና ሕዝቡን እያስረዳ በድፍረት ያስተምር ነበር። አንዳንዶች ግን እልኸኞች በመሆን የጌታን መንገድ በሕዝቡ ፊት እየተሳደቡ አናምንም ባሉ ጊዜ ከእነርሱ ራቀ፤ አማኞችንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ አዳራሽ በየቀኑ ያስተምር ነበር። ጳውሎስ ይህን ያደረገው ለሁለት ዓመት ያኽል ነው፤ በዚያም ጊዜ በእስያ የሚኖሩ አይሁድና አሕዛብ ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ።