የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 19:1-10

ሐዋርያት ሥራ 19:1-10 NASV

አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ፣ ጳውሎስ በላይኛው አገር ዐልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አግኝቶ፣ “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፣ “አልተቀበልንም፤ እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ አልሰማንም” አሉት። ጳውሎስም፣ “ታዲያ፣ በምን ተጠመቃችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት። ጳውሎስም፣ “የዮሐንስ ጥምቀትማ የንስሓ ጥምቀት ነበር፤ ዮሐንስም ራሱ ሰዎች ከርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ እንዲያምኑ ተናግሯል” አላቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በሌሎች ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያህል ነበሩ። ጳውሎስም ወደ ምኵራብ እየገባ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያሳመናቸው ሦስት ወር ሙሉ ምንም ሳይፈራ ፊት ለፊት ይናገር ነበር። አንዳንዶቹ ግን ግትር በመሆን፣ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም፤ የጌታንም መንገድ በገሃድ ያጥላሉ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ትቷቸው ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ የትምህርት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያነጋግራቸው ነበር። ይህን ማድረጉንም ሁለት ዓመት ስለ ቀጠለ፣ በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ።