የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 18:12-23

የሐዋርያት ሥራ 18:12-23 አማ05

ጋልዮስ የአካይያ ገዢ ሆኖ በተሾመ ጊዜ አይሁድ በአንድነት ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ወደ ፍርድ ሸንጎ ወሰዱትና፥ “ይህ ሰው ሕግን በሚቃወም መንገድ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ያደርጋል!” አሉ። ጳውሎስ መልስ ለመስጠት ተዘጋጅቶ ሳለ ጋልዮስ አይሁድን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የአይሁድ ወገኖች! በደል ወይም ከባድ ወንጀል ተፈጽሞባችሁ ቢሆን ኖሮ ክሳችሁን በትዕግሥት በሰማሁ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ቃላትና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ የራሳችሁ ጉዳይ ነው፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች ላይ መፍረድ አልፈልግም።” እንዲህም ብሎ ከፍርድ ሸንጎው አስወጣቸው። በዚህ ጊዜ ሁሉም የምኲራብ አለቃውን ሶስቴንስን ይዘው በሸንጎው ፊት ደበደቡት፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ጋልዮስ ደንታ አልነበረውም። ጳውሎስ ከወንድሞች ጋር ብዙ ቀኖች በቆሮንቶስ ከቈየ በኋላ ተሰናብቶአቸው ወደ ሶርያ ሄደ፤ ጵርስቅላና አቂላም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ነገር ግን ስለት ስለ ነበረበት ከመሄዱ በፊት ክንክሪያ በሚባል ቦታ ራሱን ተላጨ። ወደ ኤፌሶን በደረሱ ጊዜ ጵርስቅላንና አቂላን እዚያ ተዋቸው፤ እርሱ ግን ወደ ምኲራብ ገብቶ ለአይሁድ ንግግር ያደርግ ነበር። ረዘም ላለ ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲቈይ ቢለምኑትም እሺ አላላቸውም። ነገር ግን “የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆን ሌላ ጊዜ ወደ እናንተ ተመልሼ እመጣለሁ” አላቸውና ከኤፌሶን በመርከብ ተሳፍሮ ሄደ። ወደ ቂሳርያም በደረሰ ጊዜ ከዚያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ለቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ተመልሶ ወደ አንጾኪያ ወረደ። እዚያም ጥቂት ጊዜ ቈየ፤ ከዚህ በኋላ በገላትያና በፍርግያ ምድር ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ አማኞችን አበረታታ።