የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 18:12-23

ሐዋርያት ሥራ 18:12-23 NASV

ጋልዮስ የአካይያ ገዥ በነበረበት ጊዜ አይሁድ ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ በፍርድ ወንበር ፊት አቅርበውትም፣ “ይህ ሰው ሕጉ በማይፈቅደው መንገድ፣ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ እያሳሳታቸው ነው” አሉ። ጳውሎስ ሊናገር ገና አፉን ሲከፍት፣ ጋልዮስ አይሁድን እንዲህ አላቸው፤ “የአይሁድ ሰዎች ሆይ፤ ያቀረባችሁት ጕዳይ ስለ ዐመፅ ወይም ስለ ከባድ ወንጀል ቢሆን ኖሮ ላደምጣችሁ በተገባኝ ነበር፤ ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ በመሆኑ፣ እናንተው ጨርሱት፤ እኔ በእንዲህ ዐይነት ነገር ፈራጅ ለመሆን አልሻም።” ስለዚህ ከፍርድ ወንበር ፊት አስወጣቸው። በዚህ ጊዜ ሁሉም የምኵራቡን አለቃ፣ ሶስቴንስን ይዘው በፍርድ ቤቱ ፊት ደበደቡት፤ ጋልዮስ ግን ነገሩ ደንታም አልሰጠውም። ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ብዙ ቀን በቆሮንቶስ ተቀመጠ፤ ከዚያም ወንድሞችን ተሰናብቶ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋራ በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ። ስእለትም ስለ ነበረበት ክንክራኦስ በተባለ ቦታ ራሱን ተላጨ። ኤፌሶን በደረሰ ጊዜም ጵርስቅላንና አቂላን እዚያው ተዋቸው፤ እርሱ ራሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋራ ይነጋገር ነበር። ከእነርሱ ጋራ እንዲሰነብት በጠየቁትም ጊዜ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ነገር ግን ሲለያቸው፣ “የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ ተመልሼ እመጣለሁ” አላቸው፤ ከኤፌሶንም ተነሥቶ በመርከብ ተጓዘ። ቂሳርያም በደረሰ ጊዜ፣ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቀረበ፤ ከዚያም ወደ አንጾኪያ ወረደ። በአንጾኪያም ጥቂት ጊዜ ከቈየ በኋላ፣ ከዚያ ተነሥቶ በገላትያና በፍርግያ አገሮች ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ደቀ መዛሙርትን ሁሉ አበረታታ።