በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ጉባኤ ፊት ቆመና እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ! በሁሉም በኩል በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን ተረድቼአለሁ፤ በከተማችሁ እየተዘዋወርኩ የአምልኮ ስፍራዎቻችሁን ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ ተብሎ የተጻፈበትን የመሠዊያ ቦታ አገኘሁ፤ እንግዲህ እኔ አሁን የምነግራችሁ ስለዚሁ ሳታውቁ ስለምታመልኩት አምላክ ነው። እርሱ ዓለምንና በዓለም ያለውንም ሁሉ የፈጠረ ነው፤ የሰማይና የምድርም ጌታ ነው፤ እርሱ በሰው እጅ በተሠራ ቤተ መቅደስ አይኖርም፤ ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌሎችንም ነገሮች ለሰው ሁሉ የሚሰጥ እርሱ ስለ ሆነ ምንም ነገር አይጐድለውም፤ የሰውም ርዳታ አያስፈልገውም። እርሱ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም አደረገ፤ የተወሰኑ ዘመኖችንና የሚኖሩባቸውንም ቦታዎች መደበላቸው። ይህንንም ያደረገው ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉና በመመራመርም ፈልገው እርሱን ማግኘት እንዲችሉ ነው፤ ሆኖም እርሱ ከእኛ ከእያንዳንዳችን ሩቅ ነው ማለት አይደለም። ‘ሕይወት የምናገኘውና የምንንቀሳቀሰው፥ የምንኖረውም በእርሱ ነው፤’ ይህም የእናንተ ባለ ቅኔዎች ‘እኛ ሁላችን የእርሱ ልጆች ነን’ እንዳሉት ነው። እንግዲህ እኛ የእርሱ ልጆች ከሆንን ‘እግዚአብሔር በሰው ጥበብና አሳብ ከወርቅ ወይም ከብር ወይም ከድንጋይ የተሠራውን ቅርጽ ይመስላል’ ብለን ማሰብ አይገባንም። እንግዲህ ሰዎች በቀድሞ ዘመን ባለማወቅ ያደረጉትን እግዚአብሔር ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየአገሩ ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አዞአል፤ እርሱ በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ሁሉ ላይ በእውነት የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአል፤ ይህንንም ለሁሉም ያረጋገጠው ያን የመረጠውን ሰው ከሞት በማስነሣቱ ነው።” “ከሞት መነሣት” የሚለውን ቃል በሰሙ ጊዜ አንዳንዶች አፌዙበት፤ ሌሎች ግን “ስለዚህ ጉዳይ ስትናገር ሌላ ጊዜ እንሰማለን” አሉት። ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከጉባኤው ወጥቶ ሄደ፤
የሐዋርያት ሥራ 17 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 17:22-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos