ሐዋርያት ሥራ 17:22-33
ሐዋርያት ሥራ 17:22-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ ውስጥ ቆሞ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የአቴና ሰዎች! በሥራችሁ ሁሉ አማልክትን ማምለክ እንደምታበዙ አያችኋለሁ። በዚህም ሳልፍ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሕፈት ያለበትን የምታመልኩበትን መሠዊያችሁን አየሁ፤ እነሆ፥ እኔ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ። ዓለሙንና በእርሱም ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌላውንም ነገር ሁሉ ለሁሉ ይሰጣልና እንደ ችግረኛ የሰው እጅ አያገለግለውም። እርሱም በምድር ሁሉ ላይ ይኖሩ ዘንድ ሰዎችን ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ ይኖሩባትም ዘንድ ዘመንንና ቦታን ወስኖ ሠራላቸው። ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉት ዘንድ፤ ነገር ግን ከሁላችን የራቀ አይደለም። እኛ በእርሱ ሕይወትን እናገኛለን፤ በእርሱም እንንቀሳቀሳለን፤ በእርሱም ጸንተን እንኖራለን፤ ከመካከላችሁም፦ ‘እኛ ዘመዶቹ ነን’ የሚሉ ፈላስፎች አሉ። እንግዲህ እኛ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆን በሰው ዕውቀትና ብልሀት በተቀረጸ በድንጋይና በብር፥ በወርቅም አምላክነቱን ልንመስለው አይገባም። የቀድሞውንስ ያለ ማወቅ ዘመን እግዚአብሔር አሳልፎታል፤ ዛሬ ግን በመላው ዓለም ንስሓ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዝዞአል። በመረጠው ሰው እጅ በዓለም በእውነት የሚፈርድባትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱን ከሙታን ለይቶ በማስነሣቱም ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት መልሶአልና።” የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኩሌቶቹ አፌዙበት፤ ሌሎችም፥ “ስለዚህ ነገር በሌላ ቀን እናዳምጥሃለን” አሉት። ጳውሎስም ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ።
ሐዋርያት ሥራ 17:22-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ፤ በማናቸውም ረገድ፣ በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን አያለሁ፤ እየተዘዋወርሁ ሳለሁ፣ የምታመልኳቸውን ነገሮች ስመለከት፣ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁና፤ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ። “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፤ ስለዚህም እርሱ የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም። የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ፤ የዘመናቸውን ልክና የመኖሪያ ስፍራቸውንም ዳርቻ ወሰነላቸው። ይኸውም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈልገው ተመራምረው ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ ብሎ ነው፤ ይህም ቢሆን እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ሆኖ አይደለም፤ የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነውም በእርሱ ነውና። ከራሳችሁ ባለቅኔዎችም አንዳንዶቹ እንዳሉት፣ ‘እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን።’ “እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም። ቀደም ሲል እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን አለማወቅ በትዕግሥት ዐልፏል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ያዝዛል። በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኗልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጧል።” እነርሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ፣ አንዳንዶቹ አፌዙ፤ ሌሎች ግን፣ “ስለዚህ ጕዳይ ከአንተ ዳግመኛ ለመስማት እንፈልጋለን” አሉት። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ፤
ሐዋርያት ሥራ 17:22-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ፦ ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ። ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም። እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል። የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን፦ ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት። እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ።
ሐዋርያት ሥራ 17:22-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ጉባኤ ፊት ቆመና እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ! በሁሉም በኩል በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን ተረድቼአለሁ፤ በከተማችሁ እየተዘዋወርኩ የአምልኮ ስፍራዎቻችሁን ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ ተብሎ የተጻፈበትን የመሠዊያ ቦታ አገኘሁ፤ እንግዲህ እኔ አሁን የምነግራችሁ ስለዚሁ ሳታውቁ ስለምታመልኩት አምላክ ነው። እርሱ ዓለምንና በዓለም ያለውንም ሁሉ የፈጠረ ነው፤ የሰማይና የምድርም ጌታ ነው፤ እርሱ በሰው እጅ በተሠራ ቤተ መቅደስ አይኖርም፤ ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌሎችንም ነገሮች ለሰው ሁሉ የሚሰጥ እርሱ ስለ ሆነ ምንም ነገር አይጐድለውም፤ የሰውም ርዳታ አያስፈልገውም። እርሱ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም አደረገ፤ የተወሰኑ ዘመኖችንና የሚኖሩባቸውንም ቦታዎች መደበላቸው። ይህንንም ያደረገው ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉና በመመራመርም ፈልገው እርሱን ማግኘት እንዲችሉ ነው፤ ሆኖም እርሱ ከእኛ ከእያንዳንዳችን ሩቅ ነው ማለት አይደለም። ‘ሕይወት የምናገኘውና የምንንቀሳቀሰው፥ የምንኖረውም በእርሱ ነው፤’ ይህም የእናንተ ባለ ቅኔዎች ‘እኛ ሁላችን የእርሱ ልጆች ነን’ እንዳሉት ነው። እንግዲህ እኛ የእርሱ ልጆች ከሆንን ‘እግዚአብሔር በሰው ጥበብና አሳብ ከወርቅ ወይም ከብር ወይም ከድንጋይ የተሠራውን ቅርጽ ይመስላል’ ብለን ማሰብ አይገባንም። እንግዲህ ሰዎች በቀድሞ ዘመን ባለማወቅ ያደረጉትን እግዚአብሔር ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየአገሩ ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አዞአል፤ እርሱ በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ሁሉ ላይ በእውነት የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአል፤ ይህንንም ለሁሉም ያረጋገጠው ያን የመረጠውን ሰው ከሞት በማስነሣቱ ነው።” “ከሞት መነሣት” የሚለውን ቃል በሰሙ ጊዜ አንዳንዶች አፌዙበት፤ ሌሎች ግን “ስለዚህ ጉዳይ ስትናገር ሌላ ጊዜ እንሰማለን” አሉት። ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከጉባኤው ወጥቶ ሄደ፤
ሐዋርያት ሥራ 17:22-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ “የአቴና ሰዎች ሆይ! እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ። ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና፥ አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፤ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ ‘እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና፤’ ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን፤ እንኖርማለን። እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም። እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሓ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀንቀጥሮአልና፤ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።” የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኩሌቶቹ አፌዙበት፤ እኩሌቶቹ ግን “ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን፤” አሉት። እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ።