የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 15:22-35

የሐዋርያት ሥራ 15:22-35 አማ05

ከዚህ በኋላ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው ከጉባኤው መካከል ጥቂት ሰዎችን መርጠው ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ ስለዚህ በወንድሞች መካከል በመሪነት መልካም ዝና የነበራቸውን በርሳባስ የተባለውን ይሁዳንና ሲላስን መረጡ። የተጻፈውን ደብዳቤ በእነርሱ እጅ ላኩ፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “እኛ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞቻችሁ፥ በአንጾኪያና በሶርያ፥ በኪልቅያም ለምትኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁ ወንድሞቻችን ሰላምታ እናቀርባለን፤ ከእኛ መካከል አንዳንድ ሰዎች እኛ ሳናዛቸው ወደ እናንተ መጥተው በነገሩአችሁ ቃል እንዳስቸገሩአችሁና ግራ እንዳጋቡአችሁ ሰምተናል፤ ስለዚህ በአንድነት ከተሰበሰብን በኋላ መልእክተኞችን መርጠን ከተወደዱት ወንድሞቻችን ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ልንልካቸው ተስማማን። በርናባስና ጳውሎስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው። የጻፍንላችሁን በቃልም ጭምር እንዲነግሩአችሁ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። ከእነዚህ ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ከባድ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ መልካም ሆኖ አግኝተነዋል፤ ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብ አትብሉ፤ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋን አትብሉ፤ ደምም አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ፤ ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ብትጠበቁ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ደኅና ሁኑ።” መልእክተኞቹም ተሰናብተው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ አማኞቹንም ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጡአቸው። አማኞቹም ደብዳቤውን ባነበቡ ጊዜ በሚያጽናናው መልእክት እጅግ ደስ አላቸው። ይሁዳና ሲላስ ነቢያት ስለ ነበሩ ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጽናኑአቸው፤ አበረታቱአቸውም። ይሁዳና ሲላስ ጥቂት ቀኖች እዚያ ከቈዩ በኋላ ከአማኞች ወንድሞች ጋር ተሰነባብተው ወደ ላኩአቸው ተመልሰው ሄዱ። [ሲላስ ግን እዚያው መቅረት ፈለገ።] ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ አማኞች ጋር ሆነው የጌታን ቃል እያስተማሩና እየሰበኩ ጥቂት ቀኖች በአንጾኪያ ቈዩ።