የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 15

15
የኢየሩሳሌም ጉባኤ
1አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ሄደው፥ “ለሙሴ በተሰጠው ሕግ መሠረት ካልተገረዛችሁ ልትድኑ አትችሉም” እያሉ አማኞችን ያስተምሩ ጀመር። #ዘሌ. 12፥3፤ ሐ.ሥ. 10፥1-43። 2ጳውሎስና በርናባስ ስለዚህ ጉዳይ ከሰዎቹ ጋር ንትርክና ክርክር አደረጉ፤ ከዚህ በኋላ ጳውሎስና በርናባስ በአንጾኪያ ካሉ ከሌሎች ጥቂት ወንድሞች ጋር ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱና ጉዳዩን ለሐዋርያትና ለሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ።
3ስለዚህ እነርሱ በቤተ ክርስቲያን ተልከው ሄዱ፤ በፊንቄና በሰማርያ ሲያልፉም የአሕዛብን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ተናገሩ፤ ይህም ዜና ክርስቲያኖችን ሁሉ አስደሰተ። 4ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት፥ ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፤ መልእክተኞቹም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ ያደረገውን ሁሉ አወሩላቸው። 5ነገር ግን ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ አማኞች ተነሡና “አሕዛብ እንዲገረዙና የኦሪትን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ ይገባል” አሉ።
6ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ፤ 7ብዙ ክርክር ከተደረገም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ በእኔ አማካይነት የወንጌልን ቃል ሰምተው እንዲያምኑ ከዚህ በፊት እግዚአብሔር እኔን ከእናንተ መካከል እንደ መረጠኝ ታውቃላችሁ። 8የሰውን ልብ የሚያውቅ አምላክ፥ መንፈስ ቅዱስን ለእኛ እንደ ሰጠው ዐይነት ለእነርሱም በመስጠት መሰከረላቸው። #2፥5፤ 10፥44። 9ልባቸውን በእምነት ስላነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። 10ታዲያ፥ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በአማኞች ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ? 11እኛም የምንድነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።”
12በዚህ ጊዜ ጉባኤው ጸጥ ብሎ በርናባስና ጳውሎስ በእነርሱ አማካይነት እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ተአምርና ድንቅ ነገር ሁሉ ሲናገሩ በመገረም አዳመጣቸው። 13እነርሱ ተናግረው ካበቁ በኋላ፥ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞች ሆይ! እስቲ ስሙኝ! 14እግዚአብሔር አንድ በስሙ የሚጠራ ሕዝብን ከመካከላቸው ለመምረጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አሕዛብን እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን አስረድቶአል። 15ከዚህም አሳብ ጋር የነቢያት ቃል ይስማማል፤ ይህም እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ነው፦
16‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤
የፈረሰውንም የዳዊትን ቤት እሠራለሁ፤
ፍርስራሹንም ጠግኜ እንደገና አቆማለሁ።
17ይህንንም የማደርገው የቀሩት ሰዎችና
በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ እኔን እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ ነው፤
18ከጥንት ጀምሮ ይህን ሁሉ ያስታወቅኹ እኔ እግዚአብሔር እንዲህ እላለሁ፤’ #አሞጽ 9፥11-12።
19“ስለዚህ የእኔ አሳብ ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱትን አሕዛብ እንዳናስቸግራቸው ነው። 20ይልቅስ ‘ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብን አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ፤ ሳይታረድና ደሙም ሳይፈስ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋን አትብሉ፤ ደምንም አትብሉ’ ብለን እንጻፍላቸው። #ዘፀ. 34፥15-17፤ ዘሌ. 17፥10-16፤ 18፥6-23። 21ከጥንቱም ጀምሮ የሙሴ ሕግ በየሰንበቱ በምኲራቦች ይነበብ ነበር፤ ቃሉም በየከተማው ይሰበካል።”
የጉባኤው ውሳኔና ለአማኞች የተጻፈ ደብዳቤ
22ከዚህ በኋላ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው ከጉባኤው መካከል ጥቂት ሰዎችን መርጠው ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ ስለዚህ በወንድሞች መካከል በመሪነት መልካም ዝና የነበራቸውን በርሳባስ የተባለውን ይሁዳንና ሲላስን መረጡ። 23የተጻፈውን ደብዳቤ በእነርሱ እጅ ላኩ፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “እኛ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞቻችሁ፥ በአንጾኪያና በሶርያ፥ በኪልቅያም ለምትኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁ ወንድሞቻችን ሰላምታ እናቀርባለን፤ 24ከእኛ መካከል አንዳንድ ሰዎች እኛ ሳናዛቸው ወደ እናንተ መጥተው በነገሩአችሁ ቃል እንዳስቸገሩአችሁና ግራ እንዳጋቡአችሁ ሰምተናል፤ 25ስለዚህ በአንድነት ከተሰበሰብን በኋላ መልእክተኞችን መርጠን ከተወደዱት ወንድሞቻችን ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ልንልካቸው ተስማማን። 26በርናባስና ጳውሎስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው። 27የጻፍንላችሁን በቃልም ጭምር እንዲነግሩአችሁ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። 28ከእነዚህ ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ከባድ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ መልካም ሆኖ አግኝተነዋል፤ 29ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብ አትብሉ፤ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋን አትብሉ፤ ደምም አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ፤ ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ብትጠበቁ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ደኅና ሁኑ።”
30መልእክተኞቹም ተሰናብተው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ አማኞቹንም ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጡአቸው። 31አማኞቹም ደብዳቤውን ባነበቡ ጊዜ በሚያጽናናው መልእክት እጅግ ደስ አላቸው። 32ይሁዳና ሲላስ ነቢያት ስለ ነበሩ ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጽናኑአቸው፤ አበረታቱአቸውም። 33ይሁዳና ሲላስ ጥቂት ቀኖች እዚያ ከቈዩ በኋላ ከአማኞች ወንድሞች ጋር ተሰነባብተው ወደ ላኩአቸው ተመልሰው ሄዱ። #15፥33 አንዳንድ የብራና መጻሕፍት በ 34 ቊጥር የሚገኘውን አይጨምሩም። 34[ሲላስ ግን እዚያው መቅረት ፈለገ።] 35ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ አማኞች ጋር ሆነው የጌታን ቃል እያስተማሩና እየሰበኩ ጥቂት ቀኖች በአንጾኪያ ቈዩ።
የጳውሎስና የበርናባስ መለያየት
36ከጥቂት ቀኖች በኋላ ጳውሎስ በርናባስን “ና እንመለስና ከዚህ በፊት የጌታን ቃል ባበሠርንባቸው ከተሞች ሁሉ ያሉትን ወንድሞች እንጐብኝ፤ እንዴት እንደ ሆኑም እንወቅ” አለው። 37በርናባስም ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ከእነርሱ ጋር አብሮአቸው እንዲሄድ ፈለገ። 38ጳውሎስ ግን ይህ ሰው ከእነርሱ ጋር እንዲሄድ አልፈቀደም፤ ያልፈቀደበትም ምክንያት እሱ በጵንፍልያ ከእነርሱ ተለይቶ ስለ ቀረና ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር ስላልሄደ ነው። #ሐ.ሥ. 13፥13። 39በዚህ ምክንያት በጳውሎስና በበርናባስ መካከል ከፍ ያለ ክርክር ተነሣና ተለያዩ፤ ስለዚህ በርናባስ ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። 40ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ጳውሎስን ለጌታ ጸጋ ዐደራ ከሰጡት በኋላ ሄደ። 41እርሱም አብያተ ክርስቲያንን እያበረታታ በሶርያና በኪልቅያ በኩል አለፈ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ