አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ሄደው፥ “ለሙሴ በተሰጠው ሕግ መሠረት ካልተገረዛችሁ ልትድኑ አትችሉም” እያሉ አማኞችን ያስተምሩ ጀመር። ጳውሎስና በርናባስ ስለዚህ ጉዳይ ከሰዎቹ ጋር ንትርክና ክርክር አደረጉ፤ ከዚህ በኋላ ጳውሎስና በርናባስ በአንጾኪያ ካሉ ከሌሎች ጥቂት ወንድሞች ጋር ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱና ጉዳዩን ለሐዋርያትና ለሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ። ስለዚህ እነርሱ በቤተ ክርስቲያን ተልከው ሄዱ፤ በፊንቄና በሰማርያ ሲያልፉም የአሕዛብን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ተናገሩ፤ ይህም ዜና ክርስቲያኖችን ሁሉ አስደሰተ። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት፥ ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፤ መልእክተኞቹም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ ያደረገውን ሁሉ አወሩላቸው። ነገር ግን ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ አማኞች ተነሡና “አሕዛብ እንዲገረዙና የኦሪትን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ ይገባል” አሉ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ፤ ብዙ ክርክር ከተደረገም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ በእኔ አማካይነት የወንጌልን ቃል ሰምተው እንዲያምኑ ከዚህ በፊት እግዚአብሔር እኔን ከእናንተ መካከል እንደ መረጠኝ ታውቃላችሁ። የሰውን ልብ የሚያውቅ አምላክ፥ መንፈስ ቅዱስን ለእኛ እንደ ሰጠው ዐይነት ለእነርሱም በመስጠት መሰከረላቸው። ልባቸውን በእምነት ስላነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። ታዲያ፥ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በአማኞች ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ? እኛም የምንድነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።” በዚህ ጊዜ ጉባኤው ጸጥ ብሎ በርናባስና ጳውሎስ በእነርሱ አማካይነት እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ተአምርና ድንቅ ነገር ሁሉ ሲናገሩ በመገረም አዳመጣቸው። እነርሱ ተናግረው ካበቁ በኋላ፥ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞች ሆይ! እስቲ ስሙኝ! እግዚአብሔር አንድ በስሙ የሚጠራ ሕዝብን ከመካከላቸው ለመምረጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አሕዛብን እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን አስረድቶአል። ከዚህም አሳብ ጋር የነቢያት ቃል ይስማማል፤ ይህም እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ነው፦ ‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤ የፈረሰውንም የዳዊትን ቤት እሠራለሁ፤ ፍርስራሹንም ጠግኜ እንደገና አቆማለሁ። ይህንንም የማደርገው የቀሩት ሰዎችና በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ እኔን እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ ነው፤ ከጥንት ጀምሮ ይህን ሁሉ ያስታወቅኹ እኔ እግዚአብሔር እንዲህ እላለሁ፤’ “ስለዚህ የእኔ አሳብ ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱትን አሕዛብ እንዳናስቸግራቸው ነው። ይልቅስ ‘ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብን አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ፤ ሳይታረድና ደሙም ሳይፈስ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋን አትብሉ፤ ደምንም አትብሉ’ ብለን እንጻፍላቸው። ከጥንቱም ጀምሮ የሙሴ ሕግ በየሰንበቱ በምኲራቦች ይነበብ ነበር፤ ቃሉም በየከተማው ይሰበካል።” ከዚህ በኋላ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው ከጉባኤው መካከል ጥቂት ሰዎችን መርጠው ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ለመላክ ወሰኑ፤ ስለዚህ በወንድሞች መካከል በመሪነት መልካም ዝና የነበራቸውን በርሳባስ የተባለውን ይሁዳንና ሲላስን መረጡ። የተጻፈውን ደብዳቤ በእነርሱ እጅ ላኩ፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “እኛ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞቻችሁ፥ በአንጾኪያና በሶርያ፥ በኪልቅያም ለምትኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁ ወንድሞቻችን ሰላምታ እናቀርባለን፤ ከእኛ መካከል አንዳንድ ሰዎች እኛ ሳናዛቸው ወደ እናንተ መጥተው በነገሩአችሁ ቃል እንዳስቸገሩአችሁና ግራ እንዳጋቡአችሁ ሰምተናል፤ ስለዚህ በአንድነት ከተሰበሰብን በኋላ መልእክተኞችን መርጠን ከተወደዱት ወንድሞቻችን ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ልንልካቸው ተስማማን። በርናባስና ጳውሎስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ናቸው። የጻፍንላችሁን በቃልም ጭምር እንዲነግሩአችሁ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። ከእነዚህ ከሚከተሉት አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ከባድ ሸክም እንዳንጭንባችሁ መንፈስ ቅዱስና እኛ መልካም ሆኖ አግኝተነዋል፤ ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብ አትብሉ፤ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋን አትብሉ፤ ደምም አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ፤ ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ብትጠበቁ መልካም ታደርጋላችሁ፤ ደኅና ሁኑ።” መልእክተኞቹም ተሰናብተው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ አማኞቹንም ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጡአቸው። አማኞቹም ደብዳቤውን ባነበቡ ጊዜ በሚያጽናናው መልእክት እጅግ ደስ አላቸው።
የሐዋርያት ሥራ 15 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 15:1-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos