አንዳንድ ሰዎች ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ሄደው፥ “ለሙሴ በተሰጠው ሕግ መሠረት ካልተገረዛችሁ ልትድኑ አትችሉም” እያሉ አማኞችን ያስተምሩ ጀመር። ጳውሎስና በርናባስ ስለዚህ ጉዳይ ከሰዎቹ ጋር ንትርክና ክርክር አደረጉ፤ ከዚህ በኋላ ጳውሎስና በርናባስ በአንጾኪያ ካሉ ከሌሎች ጥቂት ወንድሞች ጋር ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱና ጉዳዩን ለሐዋርያትና ለሽማግሌዎች እንዲያቀርቡ ተወሰነ። ስለዚህ እነርሱ በቤተ ክርስቲያን ተልከው ሄዱ፤ በፊንቄና በሰማርያ ሲያልፉም የአሕዛብን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ተናገሩ፤ ይህም ዜና ክርስቲያኖችን ሁሉ አስደሰተ። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት፥ ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፤ መልእክተኞቹም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ ያደረገውን ሁሉ አወሩላቸው። ነገር ግን ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ አማኞች ተነሡና “አሕዛብ እንዲገረዙና የኦሪትን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ ይገባል” አሉ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ፤ ብዙ ክርክር ከተደረገም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ በእኔ አማካይነት የወንጌልን ቃል ሰምተው እንዲያምኑ ከዚህ በፊት እግዚአብሔር እኔን ከእናንተ መካከል እንደ መረጠኝ ታውቃላችሁ። የሰውን ልብ የሚያውቅ አምላክ፥ መንፈስ ቅዱስን ለእኛ እንደ ሰጠው ዐይነት ለእነርሱም በመስጠት መሰከረላቸው። ልባቸውን በእምነት ስላነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። ታዲያ፥ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በአማኞች ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ? እኛም የምንድነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።”
የሐዋርያት ሥራ 15 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 15:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች