የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 12:1-11

የሐዋርያት ሥራ 12:1-11 አማ05

በዚያን ዘመን ንጉሥ ሄሮድስ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ማሳደድ ጀመረ፤ የዮሐንስን ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ አስገደለው። ይህ ነገር አይሁድን ደስ እንዳሰኛቸው ባየ ጊዜ ጴጥሮስንም ደግሞ አስያዘው፤ ይህም የሆነው አይሁድ የቂጣ በዓልን በሚያከብሩባቸው ቀኖች ነበር። ጴጥሮስን ካስያዘ በኋላ ወደ ወህኒ ቤት አስገባው፤ ከአይሁድ የፋሲካ በዓል በኋላ ለሕዝቡ እስኪያቀርበው ድረስ አራት አራት ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍሮች አስረከበው። ስለዚህ ጴጥሮስ በወህኒ ቤት ተይዞ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር በጥብቅ ትጸልይ ነበር። ሄሮድስ በማግስቱ ጴጥሮስን ለሕዝቡ ሊያቀርበው አስቦ ነበር፤ ጴጥሮስም በዚያች ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ሌሎች ወታደሮችም የወህኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር። በዚያን ጊዜ የጌታ መልአክ ተገልጦ ታየ፤ በወህኒ ቤቱም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩ የጴጥሮስን ጐን መትቶ ቀሰቀሰውና “በፍጥነት ተነሥ!” አለው፤ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ላይ ወደቁ። መልአኩም “ልብስህን ልበስ! ጫማህንም አድርግ!” አለው። ጴጥሮስ እንደታዘዘው አደረገ፤ መልአኩም “ነጠላህን ልበስና ተከተለኝ!” አለው። ጴጥሮስም ወጣና ተከተለው፤ ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ ያደረገው ነገር ሁሉ እውነት አልመሰለውም። አንደኛውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ። መዝጊያውም ሰው ሳይነካው እንዲሁ ተከፈተላቸውና ወጥተው በአንድ ስላች መንገድ አልፈው ሄዱ፤ በድንገትም መልአኩ ከጴጥሮስ ተለይቶ ሄደ። ጴጥሮስም ወደ ልቡናው ተመልሶ፥ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠባበቁት ከነበረው ነገር ሁሉ ያዳነኝ መሆኑን አሁን ገና በእውነት ዐወቅሁ!” አለ።