በዚያ ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላትን እያሳደደ ያስጨንቅ ነበር፤ የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ አስገደለ። ይህ አድራጎቱ አይሁድን ደስ እንዳሰኛቸው ባየ ጊዜ፣ ጴጥሮስን ደግሞ አስያዘው፤ ይህም የሆነው በቂጣ በዓል ሰሞን ነበር። ጴጥሮስን ወህኒ ቤት ካስገባው በኋላ፣ አራት አራት ወታደሮች እየሆኑ እንዲጠብቁት በአራት ፈረቃ ለተመደቡ ወታደሮች አስረከበው፤ ይህን ያደረገውም የፋሲካ በዓል ካለፈ በኋላ ሕዝብ ፊት አውጥቶ ሊያስፈርድበት ዐስቦ ነው። ጴጥሮስም በዚህ መሠረት እስር ቤት ተጣለ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ስለ እርሱ አጥብቃ ወደ እግዚአብሔር ትጸልይ ነበር። ሄሮድስም ጴጥሮስን ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው ዐስቦ ሳለ፣ ጴጥሮስ በዚያው ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ፣ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም እስር ቤቱ በር ላይ ቆመው ነበር። የጌታ መልአክም ድንገት ታየ፤ በክፍሉም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩም የጴጥሮስን ጐን መታ አድርጎ ቀሰቀሰውና፣ “ቶሎ ተነሣ!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ሰንሰለቶቹ ከእጆቹ ወደቁ። መልአኩም፣ “ልብስህን ልበስ፤ ጫማህንም አድርግ” አለው። ጴጥሮስም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም ቀጥሎ፣ “መደረቢያህን ከላይ ጣል አድርገህ ተከተለኝ” አለው። ጴጥሮስም ተከትሎት ከእስር ቤት ወጣ፤ ነገር ግን ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ የሚያደርገው ነገር በእውን መሆኑን አላወቀም ነበር። የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ ዐልፈው ወደ ከተማዪቱ በሚወስደው መንገድ ላይ ወዳለው የብረት መዝጊያ ዘንድ ደረሱ። መዝጊያውም ራሱ ዐውቆ ተከፈተላቸው፤ እነርሱም ወጥተው ሄዱ፤ አንዲት ስላች መንገድ እንዳለፉም ወዲያው መልአኩ ተለየው። ጴጥሮስም ሲረጋጋ፣ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁድ ካሰቡብኝ ሁሉ እንዳወጣኝ አሁን ያለ ጥርጥር ዐወቅሁ” አለ።
ሐዋርያት ሥራ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 12
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 12:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos