በማግስቱ እነርሱ ሄደው ወደ ከተማው ሲቀርቡ ስድስት ሰዓት ገደማ ጴጥሮስ ወደነበረበት ቤት ሰገነት ሊጸልይ ወጣ። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ራበውና አንዳች ነገር መብላት ፈለገ፤ ምሳ በመዘጋጀት ላይ እንዳለም በተመስጦ ራእይ አየ። ያየውም ራእይ ሰማይ ተከፍቶ በአራት ማእዘን የተያዘ ትልቅ የመጋረጃ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወደ ምድር ሲወርድ ነው። በዚያም ላይ ልዩ ልዩ እንስሳት በልባቸው የሚሳቡ ፍጥረቶችና በሰማይ የሚበርሩ ወፎች ነበሩበት። በዚያን ጊዜ “ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!” የሚል ድምፅ ሰማ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ! አይሆንም! እኔ ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በልቼ አላውቅም” አለ። ደግሞም “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም” የሚል ድምፅ እንደገና ሰማ። ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ጴጥሮስ የራእዩ ፍች “ምን ይሆን?” እያለ በሐሳቡ ሲጨነቅ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች በጥያቄ የስምዖንን ቤት አግኝተው በበር ቆመው ነበር፤ ተጣርተውም “ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በእንግድነት የሚገኘው እዚህ ነውን?” ብለው ጠየቁ። ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “እነሆ! ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥና ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለ ሆንኩ ሳታመነታ ከእነርሱ ጋር ሂድ።” ጴጥሮስም ወርዶ ወደ ሰዎቹ ሄደና “እነሆ፥ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ከመቶ አለቃው ከቆርኔሌዎስ ዘንድ ነው፤ እርሱ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ የሚያከብረው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ደግ ሰው ነው፤ አንተን ወደ ቤቱ አስጠርቶ የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ገልጦ ነግሮታል” አሉት። ጴጥሮስም ወደ ቤት አስገባቸውና አስተናገዳቸው፤ ለምኖም አሳደራቸው። በማግስቱም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ በኢዮጴ ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹም አብረውት ሄዱ።
የሐዋርያት ሥራ 10 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 10:9-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos