ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፦ “በእውነት እግዚአብሔር ሰውን ከሰው እንደማያበላልጥ አስተዋልኩ፤ የማንኛውም አገር ሰው ቢሆን እግዚአብሔርን የሚፈራና ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግ ከሆነ እግዚአብሔር ይቀበለዋል። እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ቃሉን መላኩ የታወቀ ነው፤ በሁሉ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ሰላምን እየሰበከ የመጣውም ለእነርሱ ነው። ዮሐንስ ስለ ጥምቀት ከሰበከበት ጊዜ ጀምሮ ከገሊላ አንሥቶ በይሁዳ ምድር ሁሉ የሆነውን ነገር ታውቃላችሁ። “ደግሞም እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ እንደ ቀባውና ኀይልም እንደ ሰጠው ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ እርሱን መልካም ነገርን እያደረገና በዲያብሎስ የተያዙትን ሁሉ እየፈወሰ ተዘዋወረ። “በይሁዳ ገጠርና በኢየሩሳሌም ከተማ እርሱ ስላደረገው ነገር ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ እርሱን ግን በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። ነገር ግን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን ከሞት አስነሣውና እንዲገለጥ አደረገው። የተገለጠውም አስቀድሞ በእግዚአብሔር ለተመረጡት ምስክሮች ነው እንጂ ለሕዝቡ ሁሉ አይደለም፤ እርሱ ከሞት ከተነሣ በኋላ እኛ ከእርሱ ጋር አብረን የበላንና የጠጣን ምስክሮቹ ነን፤ ይህን ነገር ለሕዝቡ እንድናበሥር እርሱ በሕያዋንና በሙታን ላይ እንዲፈርድ በእግዚአብሔር የተሠየመ መሆኑን እንድንመሰክር አዞናል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኝ ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” ጴጥሮስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ ቃሉን በሰሙት ሰዎች ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስ ጋር የመጡት ከተገረዙት አይሁድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለአሕዛብ መንፈስ ቅዱስን እንደ ሰጣቸው ባዩ ጊዜ ተደነቁ። ለአሕዛብ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተሰጠ ያወቁትም አሕዛብ በሌሎች ቋንቋዎች ሲናገሩና እግዚአብሔርን በምስጋና ሲያከብሩ በመስማታቸው ነው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፤ ታዲያ፥ እነርሱ በውሃ እንዳይጠመቁ ማን ይከለክላቸዋል?” ሲል ተናገረ። ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ከእነርሱ ጋር ለጥቂት ቀኖች እንዲቈይ ለመኑት።
የሐዋርያት ሥራ 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 10:34-48
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች