ቴዎፍሎስ ሆይ! በመጀመሪያ መጽሐፌ ኢየሱስ የሠራውንና ያስተማረውን ሁሉ ጽፌአለሁ። የጻፍኩትም ኢየሱስ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ የሠራውን ነው፤ ወደ ሰማይ ያረገውም ለመረጣቸው ሐዋርያት ትእዛዙን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከሰጣቸው በኋላ ነው፤ ብዙ መከራ ተቀብሎ ከሞተ በኋላ በብዙ ግልጥ ማስረጃዎች ሕያው ሆኖ ታያቸው፤ አርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማራቸው። አብሮአቸውም በነበረ ጊዜ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “እኔ የነገርኳችሁን ከአብ የተሰጠ ተስፋ ጠብቁ እንጂ ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።” እነርሱ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፥ “ጌታ ሆይ! መንግሥትን ለእስራኤል መልሰህ የምትሰጥበት ጊዜ አሁን ነውን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜና ዘመን እናንተ ልታውቁት አትችሉም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ፥ በሰማርያ፥ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” ይህንንም ካለ በኋላ እነርሱ እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ደመናም ተቀብሎ ከዐይናቸው ሰወረው። እርሱ እያረገ ሳለ፥ እነርሱ ትኲር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች አጠገባቸው ቆመው፥ “እናንተ የገሊላ ሰዎች፥ ስለምን ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ቆማችኋል? ይህ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፥ ወደ ሰማይ ሲያርግ ባያችሁት ዐይነት ተመልሶ ይመጣል” አሉአቸው።
የሐዋርያት ሥራ 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 1:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos