ቴዎፍሎስ ሆይ፤ ኢየሱስ ለማድረግና ለማስተማር የጀመረውን ሁሉ ቀደም ባለው መጽሐፌ ጽፌልሃለሁ፤ ይኸውም እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ ለመረጣቸው ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሰጣቸው ትእዛዝ ነው። ከሕማማቱም በኋላ ራሱ ቀርቦ ሕያው መሆኑን፣ ለእነዚሁ በብዙ ማስረጃ እያረጋገጠላቸው አርባ ቀንም ዐልፎ ዐልፎ እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገራቸው። ከእነርሱም ጋር በማእድ ተቀምጦ ሳለ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ነገር ግን እኔ ስናገር የሰማችሁትን፣ አብ የሰጠውን ተስፋ ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።” እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ፣ “ጌታ ሆይ፤ የእስራኤልን መንግሥት መልሰህ የምታቋቁምበት ጊዜው አሁን ነውን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜ ወይም ወቅት ማወቁ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” ይህን ካለ በኋላ እያዩት ወደ ላይ ዐረገ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰወረችው። እርሱም በሚሄድበት ጊዜ ትኵር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ፣ እነሆ፤ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ፤ እንዲህም አሏቸው፤ “እናንት የገሊላ ሰዎች ሆይ፤ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ዘንድ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፣ ልክ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመለሳል።”
ሐዋርያት ሥራ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 1:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos