በኢየሱስ ክርስቶስ በተገኘው የሕይወት ተስፋ መሠረት በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ የተላከ፥ ለተወደድከው ልጄ ለጢሞቴዎስ፥ ከእግዚአብሔር አብና ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ለአንተ ይሁን። ዘወትር ሌሊትና ቀን አንተን በጸሎቴ ሳስታውስ አባቶቼ እንደ አደረጉት እኔም በንጹሕ ኅሊና የማገለግለውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። እንባህን አስታውሳለሁ፤ ስለዚህ በጣም ደስ እንዲለኝ አንተን ለማየት እመኛለሁ። በአንተ ያለውን እውነተኛ እምነት አስታውሳለሁ፤ እንዲህ ዐይነቱ እምነት በመጀመሪያ በአያትህ በሎይድና በእናትህ በኤውኒቄ የነበረ ነው፤ በአንተም እንዳለ ተረድቼአለሁ። በዚህ ምክንያት እጆቼን በአንተ ላይ በጫንኩ ጊዜ የተሰጠህንና እንደ እሳት ሆኖ በአንተ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንደገና እንድታቀጣጥለው አሳስብሃለሁ። እግዚአብሔር የሰጠን የኀይልና የፍቅር፥ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አይደለም። እንግዲህ ስለ ጌታችን ለመመስከር አትፈር፤ ስለ እርሱ በታሰርኩት በእኔም አትፈር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በሚሰጥህ ኀይል ስለ ወንጌል ከእኔ ጋር መከራን ተቀበል። እርሱ እኛ ስላደረግነው መልካም ሥራ ሳይሆን በራሱ ፈቃድና በጸጋው አዳነን፤ ለቅድስናም ጠራን፤ ይህንንም ጸጋ ከዘመናት በፊት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ሰጠን። ይህም ጸጋ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመምጣቱ አሁን ተገለጠ። እርሱ የሞትን ኀይል ደምስሶ በወንጌል አማካይነት ሞት የሌለበትን ዘለዓለማዊ ሕይወት ገለጠልን። እኔም የዚህ ወንጌል አብሣሪ፥ ሐዋርያ፥ አስተማሪ ሆኜ ተሾሜአለሁ። ይህን መከራ የምቀበለውም በዚህ ምክንያት ነው፤ ነገር ግን ማንን እንዳመንኩ ስለማውቅ አላፍርበትም፤ የተሰጠኝንም ዐደራ እስከዚያ ቀን ድረስ መጠበቅ እንደምችል ተረድቼአለሁ። ከእኔ የተማርከውን አስተማማኝ ቃል እንደ ምሳሌ አድርገህ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነትና ፍቅር ጠብቅ። በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የተሰጠህን መልካም ዐደራ ጠብቅ። በእስያ ያሉት ሁሉ እኔን ትተውኝ እንደ ሄዱ ታውቃለህ፤ ከእነርሱም መካከል ፊጌሉስና ሄርሞጌኔስ ይገኛሉ። ጌታ ለኦኔሲፎር ቤተሰቦች ምሕረትን ይስጥ፤ እርሱ ብዙ ጊዜ አጽናንቶኛል፤ በመታሰሬም አላፈረም። እንዲያውም ወደ ሮም በመጣ ጊዜ በትጋት ፈልጎ አገኘኝ፤ በመጨረሻው ቀን ጌታ ምሕረትን ይስጠው፤ በኤፌሶን በነበርኩበት ጊዜ ምን ያኽል እንዳገለገለኝ አንተ ራስህ ደኅና አድርገህ ታውቃለህ።
2 ወደ ጢሞቴዎስ 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ወደ ጢሞቴዎስ 1:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos